አምራች ዘርፍ ዘላቂ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት የሶስትዮሽ ትብብር ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ 05/01/2015 ዓ.ም (ኢሚ) የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ኢትዮጵያ የበርካታ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገር እየሆነች በመምጣቷ ባለፊት ሶስት ዓመታት የወጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ፣ በግሉ ዘርፉ የሚመራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ጥልቅና ጥብቅ የማሻሻያ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

በማክሮ ኢኮኖሚ ለውጥም የወጭና ገቢ ምጣኔን በማስተካከል፣ የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር፣የፋይናንስ አቅርቦትንና ዘላቅ ብድርን በማረጋገጥ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት እንድትሆን ለማስቻል የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያና የአስር ዓመት የልማት እቅድ ተግባራዊ እየተደረጉ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

የንግድ ሥራ አመችነት ለማረጋገጥ እና የገበያ ክፍተቱን ለመሙላት ተቋማዊና መዋቅራዊ የማሻሻያ ስራዎች በመተግበር ላይ እንደሆነም አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል፡፡

አክለውም መንግስት ኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ መዳረሻና ተምሳሌት ሀገር በማድረግ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ለማስፋፋት አስፈላጊውን ህግና ስርዓት በመዘርጋት መሰረተ ልማቱን እያሟላ ነው ብለዋል።

በ2020 እ.ኤ.አ የተከለሰው የኢንቨስትመንት ህግ ለወጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አዲስ አማራጭ የከፈተ በመሆኑ አዳዲስ የዘርፉ አልሚዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውንም ገልፀዋል

Share this Post