ዳያስፖራዎች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በስፋት እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል /አቶ መላኩ አለበል/

ጥር 15/2015ዓ.ም (ኢ.ሚ) በውጪ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በስፋት በመሰማራት ሀገራቸውንና እራሳቸውን እንዲጠቅሙ ምቹ ሁኔታ መኖሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል።

ዳያስፖራዎችና ባለሀብቶች የተሳተፉበት "ኢትዮጵያ ታምርት" የኢንቨስትመንት ፎረም በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።

በፎረሙ ላይ የኢንደስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደተናገሩት "ኢትዮጵያ ታምርት" በሚለው ሀገር አቀፍ መርሃ-ግብር የኢንዱስትሪ ዘርፉን እድገት ለማሳለጥ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደግ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ገልጸው፣ አሁን የሰፈነው ሰላም የዘርፉን እንቅስቃሴ ለማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

"ባለፉት ዓመታት የሀገሪቱ ኤክስፖርት ምርት እያደገ መጥቷል" ያሉት ሚኒስትሩ፣ የኢንዱስትሪዎች ማደግ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዳያስፖራዎች በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማፋጠን ባለፈ ለወጪ ምርቶች ማደግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።

"ለቀጣይ አምስት ዓመታት በተነደፈው ሀገራዊ የኢንዱስትሪ እድገት ስትራቴጂ መሰረት ለዘርፉ እድገት ርብርብ ይደረጋል" ያሉት አቶ መላኩ፣ ለስኬቱ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ተሳትፎም ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

በተለይ በውጪ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በስፋት ተሰማርተው ሀገራቸውንና እራሳቸውን እንዲጠቅሙ ምቹ ሁኔታ መኖሩን አንስተዋል፡፡

በአማራ ክልል 6 የኢንዱስትሪ አካባቢዎች ተለይተው መደራጀታቸውን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ሲሆኑ ባላፉት ስድስት ወራት በክልሉ ከ344 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 2ሺህ 575 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል ነው ያሉት።

ባለሀብቶቹ በቀጣይ ወደ ሥራ ሲገቡ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩም አመልክተዋል።

"ኢትዮጵያ ታምርት" በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም የከተማዋን የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚያስተዋውቅ ጥናታዊ መረጃ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

በኢንቨስትመንት ፎረሙ ላይ የፌዴራል፣ የክልል እና የጎንደር ከተማ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ባሀለብቶችና በውጪ ሀገር የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ተሳትፈዋል።

Share this Post