በሉማሜ ከተማ “ኢትዮጵያ ታምርት” የኢንቨስትመንት ጉብኝት እየተካሄደ ነው

ጥር 19/2015(ኢ.ሚ) በምስራቅ ጎጃም ዞን ሉማሜ ከተማ “ኢትዮጵያ ታምርት” የኢንቨስትመንት ጉብኝት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ታምርት የጉብኝት መርሃ ግብር ዓባይ የቆርቆሮ እና ሚስማር ፋብሪካን በመጎብኘት ዛሬ ተጀምሯል።

የዞኑ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ሙሉነሽ ውበቴ በእዚህ ወቅት እንዳሉት፣ በዞኑ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 1ሺህ 790 ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ተሰማርተዋል።

ከእነዚህ ባለሃብቶች ውስጥ 500 የሚሆኑት ወደ ማምረት የተሸጋገሩ ሲሆን ከ85 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖችም ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ገልፀዋል።

በ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄም በዞኑ ያሉ ኢንዱስትሪዎች የበለጠ እንዲነቃቁና በሙሉ አቅማቸው ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ሃላፊዋ ተናግረዋል።

የዓባይ ቆርቆሮ እና ሚስማር ማምረቻ ፋብሪካ ባለቤት አቶ ሽኩር አሳቡ እንዳሉት፣ ፋብሪካው ከሁለት ዓመት በፊት ወደማምረት ሥራ ገብቶ ምርቶቹን ለገበያ እያቀረበ ይገኛል።

ፋብሪካው በ7ሺህ 800 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በ25 ሚሊዮን ብር መገንባቱን ጠቁመው፣ “በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ ካፒታሉ 120 ሚሊዮን ብር ደርሷል” ብለዋል።

እንደ አቶ ሽኩር ገለጻ ፋብሪካው ለ112 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፣ በቀጣይም የበለጠ ምርታማ ለመሆን በትኩረት እየተሰራ ነው።

ዶክተር ይልቃልና ሌሎች የክልል እና የዞን አመራሮች እንዲሁም ባለሃብቶች በተገኙበት ትናንት በደብረ ማርቆስ ከተማ በ”ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ውይይትና ጉብኝት መካሄዱ ይታወሳል፡፡

Share this Post