ኢትዮጵያ በ2024 የብሪክስ አጋርነት ለአዲሱ የኢንዱስትሪ አብዮት መድረክ ላይ ተሳታፊ ሆናለች

የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በ2024 የብሪክስ አጋርነት ለአዲሱ የኢንዱስትሪ አብዮት መድረክ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ኢትዮጵያ በብሪክስ ጥምረት መካተቷ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ትልቅ ምዕራፍ ነው ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ አጋርነቱ ለውጪ ኢንቨስትመንት በተለይም በመሰረተ ልማት ፣ለአምራች ኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች በርካታ እድሎችን ይፈጥራል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከብሪክስ ማዕቀፍ ጋር የጀመረችው ጥምረት አዳዲስ የገበያ እድሎችን በመፍጠር፣ ዘመናዊና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማግኘት እድልን በማሳደግ ፣ አዳዲስ ፈጠራ እና ዘላቂ ልማትን በማጎልበት ረገድ ትልቅ አቅም አለው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በብሪክስ ውስጥ ያለው ትብብርም ከሀገራዊ የልማት ግቦቻችን ጋር የሚጣጣም እና በኢንዱትሪሊያዜሽን ፣ የስራ እድል ፈጠራ በኢኮኖሚ ብዝሃነት ላይ ያተኮረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአጋሮቻችንን እውቀት፣ ልምድና ግብአት በመጠቀም መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ለመሰለፍ ጥረታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ አክለዋል፡፡

የሀገራችን የኢንዱትሪ ፖሊሲ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ፣የማምረት አቅምን በማሳደግ እና ዘላቂ ልማትን በማምጣት ላይ ያተኮረ ነው ያሉት አቶ ታረቀኝ የ2024 የብሪክስ አጋርነት ለአዲስ የኢንዱስትሪ አብዮት ኢትዮጵያ ከፍተኛ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ፣የኢንዱስትሪ እድገትን ለማምጣት እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት እድታስመዘግብ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

Share this Post