“የወጪ አገራት ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የሚደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው” -- ቋሚ ኮሚቴው

ግንቦት 15፣ 2016 ዓ.ም(ኢሚ) በውጪ ምንዛሬ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትን የኢንዱስትሪ ምርቶች በአገር ውስጥ ለመተካት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አማረች ባካሎ (ዶ/ር) የሀገር ውስጥ ምርቶችን በሚገባ ማስተዋወቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።

ማህበረሰቡ ለአገር ውስጥ ምርቶች ያለውን ግምት ከፍ እንዲል የሚያደርጉ ሥራዎችም መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ማስተሳሰር ፣ ወጣቶችን ማብቃትና ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻልባቸውን መንገዶች ማጤን ይገባል ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት በጥናትና ምርምር ለመፍታት የሚያደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው ተብሏል።

ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ሥራ ፈጣሪዎችን ማበረታታትና ተደራሽ መሆን እንደሚገባ ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል፡፡

ለኢንዱስትሪው የሚፈሰው የሀገር ኃብት በፍትሃዊ መንገድ ለታለመለት ዓላማ መዋሉንና ተገቢውን ውጤት እያስመዘገበ ነው የሚለውን መመዘን አለበት ብለዋል ሰብሳቢዋ፡፡

የኢንዱስትሪዎችን ወቅታዊ መረጃ የሚያሳዩ ዲጂታል መረጃዎችን ማደራጀት እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው ለኢንዱስትሪዎች በተለያዩ አማራጮች ፈሰስ የሚደረገው ኃብት ብድር የመመለስ አቅም እሴት የመጨመርና ኤክስፖርትን የመተካት የሚሉ መመዘኛዎች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ በ ኦን ላይን በመሰጠት ላይ ይገኛል ፣ የመሬትና መሠረተ ልማት ጉዳዮች አሁንም ትኩረት ይሻሉ ብለዋል።

በቆዳው ዘርፍ ላይ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ የተዘጉ ኢንዱስትሪዎችን የመታደግና የገበያ ሰንሰለቱን የማሳጠር ሥራ እየተሳራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት እንዲደረግና የሰራተኞች ዝቅተኛ መነሻ የደሞዝ ተመን መዘጋጀት እንደሚገባው ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

ኢትዮጵያ_ታምርት #እኛም_እንሸምት

Share this Post