ዓለም አቀፍ የጸረ-ሙስና ቀን "ትወልድን በስነ-ምግባር ተቋምን በአሰራር" በሚል መሪ ቃል ተከበረ፡፡

ህዳር 23/2018 ዓ.ም (ኢሚ)የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን ዓለም አቀፍ የጸረ-ሙስና ቀን "ትወልድን በስነ-ምግባር ተቋምን በአሰራር" በሚል መሪ ቃል አከበሩ፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ‎ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንደገለፁት ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪ የበለፀገች እንድትሆን የማምረት አቅም አጠቃቀማችንን ከፍ በማድረግ ኢንዱስትሪው በቀጣይ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ መምራት የሚችልበት አውድ በመፍጠር የፖሊሲ፤ የኃይል፤ የፋይናስ ችግሮችን በቅርበት በመፍታት ውጤታማ የሚሆኑበትን መንገድ አመቻችተናል ሲሉ ገልፀዋል ፡፡

ይህን ስኬታማ ጉዞ ለማስቀጠል ሀገራችን ከሙስና የፀዳች እና ሁሉንም ዜጋ እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት በማቋቋምና ልዩ ልዩ አሰራሮችን በመዘርጋት እየተሰራ እንደሆነ ገልጸው ሙስና በሀገር እና ህዝቦች ላይ ውድቀት የሚያስከትል አደገኛ ወንጀል በመሆኑ ሙስናን የሚፀየፍ ቤተሰብ፣ ማህበረሰብ እና ሀገር መገንባት እንደሚገባ እና የምንስራቸውን ስራዎች ግልፅ እና አሳታፊ በማድረግ አመራሩ እና ሰራተኛው ተናቦ የተሰጠውን ሀገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ይገበዋል ብለዋል፡፡

የስነምግባርና ፀረ-ሙስና ኮምሽን ምክትል ኮምሽነር አቶ ፈቃዱ ሰቦቃ በበኩላቸው ለቀጣይ ትውልድ የተሻለ ሀገር ለማውረስ ትውልዱ ላይ መስራት የእያንዳዱ ዜጋ ኃላፊነት ነው፡፡ የሙስና መንስኤዎች በርካታ ቢሆኑም ዋነኛው መንስኤ የአመለካከት መዛነፍ መሆኑን አውስተው ይህንን ለማረም የሚያስችል ተቋም ገንብተን ለኢትዮጵያ ትልቅ መሰረት እየጣልን እንገኛለን ለዚህም ስኬት መልካም ሥነምግባር የተላበሱ አመራርና ሠራተኞች ሥነምግባራዊ ተቋምን በመፍጠር ፍትሃዊ እና የበለፀገ ማህበረሰብ የመፍጠር ዕድሉ ሰፊ ነው ብለዋል።

ንቅናቄው በዋናነት በሥነምግባር እና በኃላፊነት የሚመራ ትውልድ ማሳደግ፣ በብቃትና ግልጽ በሆኑ ሂደቶች የሚሰሩ ተቋማት መገንባት፣ ባለድርሻ አካላትን በሙስና ትግል ንቁ ተሳታፊ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ማስቻልና መሪዎች እና ዜጎች የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ማረጋገጥ እንደሆነም ገልጸዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ሰነድ በመርሐግብሩ ላይ ለተገኙ የኮሚሽኑ ተወካዮች ርክክብ ተፈፅሟል ።

በመድረኩም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፤ አምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ከፍተኛ ኃላፊዎች እና ሰራተኞች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

Share this Post