ከ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ወዲህ የታየው የአምራች ኢንዱስትሪ መነቃቃት አበረታች ነው፡- ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

ግንቦት 6/2016ዓ.ም(ኢ.ሚ)ከ“ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ወዲህ የታየው የአምራች ኢንዱስትሪ መነቃቃት አበረታች ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

ክልሉ የአምራች ኢንደስትሪውን እንደአንድ የትኩረት አቅጣጫ ወስዶና በዘርፉ ያሉትን ተግዳሮቶችና ዕድሎች ለይቶ መንቀሳቀሱ ለተጀመረውንቅናቄ ጉልበት እንዲሆነው እያስቻለ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።

የክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪ የኢንቨስትመንት ንቅናቄ ግልፅ ስትራቴጂና ግብ ያለው ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፤ በዚሁ መሠረት ብዙ የስራ ዕድሎችን በመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሬ በማሳደግ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ እንዲሁም የሀገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታት ረገድ ሰፊ ስራ በማከናወን ላይ እንገኛለን፤ አበረታች ውጤቶችም ተመዝግቧል ብለዋል።

የተለያዩ የምክክር መድረኮችን በመፍጠር የአምራች ኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር መቻሉን ጠቅሰዋል።

በዘርፉም የሚስተዋሉ የፋይናንስ፣የመሠረተ ልማት፣ የግንባታና የምርት ግብአቶች ማነቆዎች ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ እንደተቻለ ገልጸው፤በውጤቱም ብዙ ኢንዱስትሪዎች በተነቃቃ አካኋን ወደ ምርት ተመልሰዋል ነው ያሉት።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በዚህ የስኬት ጉዞ፣ ከምንም በላይ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነት ጨምሯል፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት እየሰፋ ሄዷል።

በሌላ በኩል ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን በመጥቀስ፤ ስለዘርፉ ያለው ግንዛቤም መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል።

ይህም የአምራች ኢንዱስትሪው ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ድርሻውን እንዲያሳድግ አስችሎታል ነው ያሉት፡፡

ይህ ማለት ግን የዘርፉ ጉዞ በሚፈለገው ፍጥነት ላይ ደርሰናል ማለት አይደለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በቀጣይ የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄን በመጠቀም በነባር በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዙሪያ ያሚስተዋሉ ያልተቀረፉ ማነቆዎችን ለይተን ለመፍታት እንዲሁም ለአዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የምንሰራ ይሆናል ብለዋል።

Share this Post