የቡሬ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪን በተሟላ አቅም ወደ ልማት ለማስገባት በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው (አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር)
ሚያዚያ 27/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የቡሬ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪን በተሟላ አቅም ወደ ልማት ለማስገባት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ከተሞች ልማት ክላስተር አስተባባሪና ከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን መሐመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የአማራ ክልል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በቡሬ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ውስጥ ከገቡ አልሚ ባለሀብቶች ጋር ባካሄደው መድረክ የተገኙት ዶክተር አሕመዲን መሐመድ ግብዓትና የኃይል አቅርቦት ለኢንዱስትሪ ምርታማነት አቅም መሰረታዊ ጉዳይ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
በዚህም በ260 ሔክታር መሬት ላይ በለማው የቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሰባት የገጠር ሽግግር ማዕከላትን ጨምሮ ምቹ የመሠረተ ልማት መዘርጋቱን ገልጸዋል።
በቀጣይም የቡሬ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪን በተሟላ አቅም ወደ ልማት በማስገባት ለአልሚ ባለሃብቶች ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
መድረኩ የቡሬ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ያለበትን ሁኔታ ለመረዳት፣ ለመማማርና ልምድ ለመቀያየር እንዲሁም በስራ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍትሔ ለመስጠት የሚረዳ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመሠረተ ልማትና አቅም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አድማሱ ይፍሩ፥ መንግስት የቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ ለኢንዱስትሪ ምርታማነት አቅም የሆኑ ፓርኮች መገንባታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በቡሬ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ የሚስተዋሉትን የኃይል አቅርቦትና ተያያዥ ችግሮች መፍትሔ በመስጠት ወደተሟላ የምርታማነት አቅም ለማስገባት ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
ባለሀብቶችም ከሀይል አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚያነሱት ጥያቄ በቀጣይ የሚቀረፍ መሆኑን በመገንዘብ በሙሉ አቅም ወደስራ ለመግባት ዝግጁ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብርሃኑ ጣምያለው፥ በክልሉ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ አቅም የሚሆን ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት መኖሩን ገልጸዋል።
በዚህም ክልሉን የኢንዱስትሪ ማዕከል ማድረግ የሚያስችሉ የኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በቀጣይም የቡሬ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ በሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የተሰማሩ አልሚዎችን ወደተማላ የማምረት አቅም ለማሸጋገር ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግ አንስተዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አመራሮች፣በቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዳስትሪ በኢንቨስትመንት የገቡ ባለሃብቶችና የልማት አጋሮች ተገኝተዋል።
#ኢትዮጵያ_ታምርት
#እኛም_እንሸምት