የኢትዮጵያን ነፃነት ለማስጠበቅ የተከፈለውን መስዋዕትነት በልማት ስኬት መድገም ይገባል-አባት አርበኞች

ሚያዚያ 28/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የኢትዮጵያን ነፃነት ለማስጠበቅ የተከፈለውን መስዋዕትነት ትውልዱ በልማት ስኬት መድገም እንደሚገባው አባት አርበኞች አስገነዘቡ።

አባት አርበኞቹ 3ኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በጎበኙበት ወቅት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ትውልዱ የሚያኮራ ታሪክ እየሰራ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በኤክስፖው በተለይም የስራ እድል መፍጠር የሚችሉና ሀገሪቱን ሊያሻግሩ የሚችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በተጨባጭ ተመልክተናል ነው ያሉት።

አባት አርበኞቹ በተለያዩ አውደ ውጊያዎች በመሳተፍ አኩሪ ገድል ማስመዝገባቸውን አስታውሰው፤ የአሁኑ ትውልድ በልማት የራሱን የጀግንነት ታሪክ እየፃፈ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላችው፥ ጀግኖች አርበኞች የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር የከፈሉት መስዋዕትነት ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የአሁኑ ትውልድ ኢትዮጵያን ከድሕነት ሊያወጡ በሚችሉ የልማት ተግባራት ላይ በመሳተፍ የሀገሩን ብልጽግና ማረጋገጥ ይጠበቅበታል ብለዋል።

አባት አርበኞች በዘመናቸው የራሳቸውን የጀግንነት ገድል እንደፈፀሙ ሁሉ ቀጣዩ ትውልድ የራሱ የሆነና የሚኮራበትን ታሪክ መስራት አለበት ብለዋል።

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እውን ማድረግ ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ፥ የአሁኑ ትውልድ አርበኝነት ከምርታማነት ጋር መያያዝ እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በተለይም ኋላቀርነትን በማስወገድ እና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት በማምረት ድሕነትን መዋጋት እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post