የኢትዮጵያ አምራች ዘርፉ የሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት አንቀሣቃሽ ሞተር ነው (አቶ አፍራካ ዘለቀ)
መጋቢት 04/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ፕሮጀክት ያዘጋጀው የኢንቨስትመንትና የግሉ ዘርፍ የአቅም ልማት ስልጠና ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሀገር አቀር የዘርፍ ማህበራት ዋና ፀኃፊ አቶ አፍሪካ ዘለቀ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ የሀገር ውስጥ ሀብት በማመንጨት፣ መሠረታዊ ሸቀጦችንና አገልግለቶችን በማቅረብ፣ ለፈጠራና አዳዲስ ግኝቶች መሠረት በመጣል፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ተወዳዳሪነትን በማጎልበት የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ አቅም በመገንባት የላቀ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።
የአምራች ማህበራት በአንፃሩ የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት ከመሆናቸውም በላይ የሙያ እኩልነትና ትስስር እንዲኖር፥ በመንግሥትና በግሉ ዘርፉ መካከል የጋራ ራዕይ እና የዳበረ ግንኙነት እንዲመሠረት፣ የማምረት ሥራ እና የገቢያ ዕድል እንዲስፋፋ የሙያ ብቃት እንዲጎለብት፤ እንዲሁም መልካም የንግድ ሥነ ምግባር እንዲስፋፋ ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ እንደሚገኙ የገለፁት አቶ አፍሪካ የአምራች ዘርፍ ማህበራት ሀገራዊ አዎንታዊ አበርክቷቸውን ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰዋል ።
የአምራች ዘርፋ ልማት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች የድኅነት ማስወገጃ ስልት ብቻ ሣይሆን የማኅበራዊና ፖለቲካዊ መረጋጋትን ለመፍጠር ጉልህ ሚና ያለው ዘርፍ ነው ያሉት ዋና ፀኃፊው የኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊውን ምርት በጥራትና በበቂ መጠን አምርተው በማቅረብ የሸማቹን ፍላጎት በማሟላት እና ኅብረተሰቡ የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር በማድረግ በሀገራችን ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የሚመለከተው ሁሉ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል ።
የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ከመንግሥት ጋር የሚያደረጉት የውይይት እና የሥልጠና መድረክ መንግሥት የአምራቹን ዘርፍ ችግሮች እና ፍላጎቶች ለመረዳትና መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የዘረጋቸውን የፖሊሲና አስተዳደራዊ መመሪያዎችን ተገንዝበው እንዲንቀሳቀሱ ግልፅነትና ተጠያቂነትን ያሰፈነ የአሠራር ስርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
#ኢትዮጵያ_ታምርት
#እኛም_እንሸምት