ኢነርጂ ኦዲት ኃይልን በብቃትና በአግባቡ ያለብክነት ጥቅም ላይ ለማዋል ወሳኝ ስራ ነዉ (አቶ ይመኑ አለኸኝ)
መጋቢት 08/2017 ዓ.ም (ኢሚ) አምራች ኢንዱስትሪዎች (አንድን ምርት ለማምረት የሰዉ ኃይል፣ የጥሬ እቃ እና የኢነርጂ ወጭዎቻቸው ከፍተኛዉን ድርሻ ይይዛሉ ያሉት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ሴክተር ሪፎርም ፐርፎርማንስ ፕሮጀክት የኢነርጅ ኢፊሸንሲ ባለሙያው አቶ ይመኑ አለኸኝ የኢነርጂ አጠቃቀምን ለማሻሻል የመጀመሪያዉ ተግባር አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚጠቀሙትን የኃይል መጠን መለካት መሆኑን በመጥቀስ የኃይል መቆራረጥ ፋብሪካዎች የሚያገኙትን ኢነርጂ በብቃት መጠቀም ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ቢኖረዉም ያገኙትን ኃይል ሳያባክኑ በጥራት መጠቀም ላይ ያሉባቸውን ክፍተቶች ማሻሻል ላይ ትኩረት አድርገው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪዎች የኢነርጂ አጠቃቀማቸዉን በለኩ ቁጥር ጥቅም ላይ የዋለዉንና የባከነዉን የኃይል መጠን ማወቅና ብክነቱን መቀነስ የሚያስችሉ የማሻሻያ ስልቶችን ይለያሉ ያሉት አቶ ይመኑ የኢነርጂ ኦዲት ኃይልን በብቃትና በአግባቡ ያለብክነት ጥቅም ላይ ለማዋል ወሳኝ ስራ ነዉ፡፡
ባለፉት ዓመታት የኢነርጂ ኦዲት በሰራንባቸዉ ከፍተኛ ኃይል በሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ላይ የሚባክነዉ የኢነርጂ መጠን እጅግ ከፍተኛመሆኑን የገለጹት ባለሙያው ለማሳያነት ከ8 ሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎች የተገኘዉ የኢነርጂ የብክነት መጠን በብር ሲሰላ ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ፣ ከሁለት ሳሙና ፋብሪካ ከ 7.7 ሚሊዮን ብር በላይ፣ ከሁለት የፓኬጂንግ ፋብሪካ ከ4.7 ሚሊዮን ብር በላይና ከአንድ ወረቀት ፋብሪካ ከ4.5 ሚሊዮን ብር በላይ ኢነርጅ በየዓመቱ ይባክናል ብለዋል፡፡
የኢንርጅ አጠቃቀም ብክነትን በመቀነስ የተሳለጠ የኃይል አጠቃቀም ስርዓትን ዕውን ለማድረግ ለአምራቾች ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ስራ መስራት ፤ የኢነርጂ አጠቃቀም ኦዲትና ኢፊሸንሲ ስራን የሚሰራ የሰለጠነ የሰዉ ኃይል መፍጠር፤ የኢነርጂ ኢፊሸንሲ ማበረታቻ ፓኬጅ ስርዓት መዘርጋትና የኢትዮጵያ ፔትሮሊየምና ኢነርጂ ባለስልጣን ከሚመለከታቸው የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ስራውን በቅንጅት መስራት ቢቻል የኢነርጅ አጠቃቀም ብክነትን በመቀነስ ያለምንም ጥቅም የሚባክነውን የሀገር ሃብት ማዳን እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የኢነርጂ አጠቃቀም ማሻሻል የኃይል መቆራረጥን ለማስቀረት ሌላው አማራጭ ነውም ብለዋል፡፡
#ኢትዮጵያ_ታምርት
#እኛም_እንሸምት