የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲው ለወጭና ተኪ ምርት ተመጣጣኝ ትኩረት መስጠቱ እምርታዊ ለውጥ እያመጣ ነው (አቶ መሳይነህ ውብሸት )

መጋቢት 16/2017 ዓ.ም (ኢሚ) ከ22 ዓመታት በላይ በስራ ላይ የነበረው የዘርፉ ስትራቴጅ ትኩረቱ የውጭ ባለሃብቶችና የወጭ ምርቶች ላይ የነበረ መሆኑን ያስታወሱት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተኪ ምርቶች ተወዳዳሪነት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ መሳይነህ ውብሸት ስትራቴጅው በአዲስ ፖሊሲ ሲሻሻል ለተኪ ምርትና ወጭ ምርቶች ተመጣጣኝ ትኩረት የሰጠ በመሆኑ ከውጭ የሚገቡ ያለቀላቸውን የኢንዱስትሪ ምርቶች በሀገር ውስጥ ለመተካት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ስትራቴጅክ ተኪ ምርቶችን በመለየት ወደ ስራ በመገባቱ ለአምራቾች የስራ ማስኬጃ የገንዘብ የብድር አቅርቦት፣ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር ተያይዞ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ችግሮችን መፍታት መቻሉን የገለፁት መሪ ስራ አስፈፃሚው በተሰማሩበት ዘርፍ የመፈፀም ክፍተት ላለባቸውን አምራቾች ተከታታይነት ያለው የአቅም ልማት ስልጠና በመስጠትና የቅርብ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ውጤታማነታቸውን ለማሻሻል እየተሰራ ስለመሆኑ ጠቁመዋል ።

የተኪ ምርት ስትራቴጂው ወደ ተግባር መግባት መቻሉ የዘርፉን የሀገር ውስጥ ገበያ ድርሻ ከፍ እንዲል ፣ የማምረት አቅም አጠቃቀም እንዲሻሻል፣ የስራ ዕድል ፈጠራ ከፍ እንዲልና የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ መጠን ማዳን እንዲቻል ማድረጉን የገለፁት አቶ መሳይነህ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረትና ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ 2ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ማዳን መቻሉን እንደ ማሳያነት ጠቅሰዋል ።

የምናመርታቸው ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ ፤ የምርት ምጣኔያቸው ከፍ እያለ በመጣ ቁጥር አለማቀፋዊ ተወዳዳሪነታችንን የማሳደግ እድሉ ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ መሳይነህ የተኪ ምርቶች የገበያ ድርሻ ከፍ እያለ መምጣቱ የሚያሳየው ህዝባችን በራሱ ምርት የመጠቀም ባህሉ እየተሻሻለ መምጣቱን የሚጠቁም ቢሆንም በራሱ ምርት በኩራት መጠቀም የማይችል ህዝብና ሀገር መለወጥ የማይችል በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በራሱ ምርት በኩራት በመጠቀም የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን ለሚመለከተው አስተያየት በመስጠት ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ምንፈልገው ለውጥ መምጣትና ሌሎች ሀገራት የእኛን ምርት የሚጠቀሙ እንዲሆኑ በማድረጉ ለዓለማቀፋዊ ጥራትና ተወዳዳሪነት የሚተጋ ውጤታማ ዘርፍ መገንባት እንችላለን ብለዋል።

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post