እንደ ሃገር የአምራች ዘርፉን ማሳደግ የምንችለው አነስተኛ እና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ላይ ስንሰራ ነው( አቶ መላኩ አለበል)
መጋቢት 19/7/2017ዓ.ም (ኢሚ) የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት አፈፃፀም ዙሪያ ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ ፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት ሲታሰብ በዋናነት አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ዋነኛ መሰረቶች ናቸው ብለዋል፡፡
አስተማማኝ የፋይናንስ አቅርቦት የኢንተርፕራይዞችን ዘላቂነትና ተወዳዳሪነት ከማሳደግ አኳያ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
እንደ ሃገር የአምራች ዘርፉን ማሳደግ የምንችለው አነስተኛ እና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ላይ ስንሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ ይህን ማምጣት የምንችለው ለዜጎች ዘላቂ የስራ እድል መፍጠር እና አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን በአግባቡ መደገፍና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በትኩረት መስራት ስችል ነው ብለዋል ፡፡
በኢንዱስትሪ በበለፀጉ ሃገራት በስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛውን ድርሻ የሚዙት በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ በሀገራችን ባለፉት ጥቂት አመታት ዘርፉን ለመደገፍ የተለያዩ ስራዎችን በተለይ የፖሊሲና የአሰራር ማሻሻያዎች መደረጋቸውን እና በኢትዮጵያ ታምርት ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል፡፡
በመቀጠልም በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናስ ፕሮጀክት አስተባባሪ ወ/ሮ የመንዝወርቅ ግርፌ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፕሮጀክት ስኬት ምን እንደሚመስል ለባለድርሻ አካላት ገለፃ አድርገዋል ፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ብሔራዊ ባንክ ፤ ልማት ባንክ ፤ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት እና ገንዘብ ሚኒስቴር የተውጣጡ ባለሙያዎች ስለተደረገላቸው ገለፃ አመስግነው ፕሮጀክቱ የተያዘበት መንገድ በጣም ጥሩ መሆኑን ለማየት ችለናል ብለዋል ፡፡
የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክቱ ላለፉት ስምንት አመታት በአለም ባንክ እና በአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ 476 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ የተደረገለት ስለመሆኑና 7250 ለሚሆኑ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በሊዝ እና በስራ ማስኬጃ ብድር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉ ተጠቅሷል ፡፡
#ኢትዮጵያ_ታምርት
#እኛም_እንሸምት