የአምራች ዘርፉን ችግሮች በመለየት ዘላቂ የመፍትሄ እርምጃዎች ለማምጣት ከተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራ ነው (አያና ዘውዴ (ዶ/ር)
መጋቢት 19/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የክላስተሮች የ2017 በጀት ዓመት የ8 ወራት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ላይ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊ አያና ዘውዴ (ዶ/ር) ለዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ሃገራዊ ሥርዓት በመዘርጋት አምራች የኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማሳዳግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ዘርፉ ለሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ስኬትና መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን ተኪ የለሽ ሚና እንዲወጣ ለማስቻል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በየደረጃው ባለቤት ኖሯቸው እየተሰራ መሆኑን ያነሱት የፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊው የአምራች ዘርፉን ችግሮች በመለየት ዘላቂ የመፍትሄ እርምጃዎች ለማምጣት ከተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በተለይም በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተመዘገቡ ውጤዎች ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የብድርና ግብዓት አቅርቦት ማሳደግ፣ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ወደ ምርት በማስገባት በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
መሰረተ ልማት ፣ ኢንቨስትመንት ፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ አማካይ የማምረት አቅም አጠቃቀምን ማሳደግ መቻሉን የገለፁት አያና ዘውዴ (ዶ/ር) አምራች ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚው ዕድገት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
#ኢትዮጵያ_ታምርት
#እኛም_እንሸምት