በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ስራ የተመለሱ ኢንዱስትሪዎች የሚዲያ ባለሙያዎች የመጀመሪያ ዙር ጉብኝት እየተካሄደ ነው
መጋቢት 26/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአዲስ አበባ እና ሸገር ሲቲ ከተማ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ስራ የተመለሱ ኢንዱስትሪዎችን በመጎብኘት ላይ ናቸው።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር በቀል አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደጉ ይታወቃል።
ንቅናቄው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በጥራትና በብዛት ለማምረት እንዲሁም የግብርና እና ማዕድን ምርቶች ላይ ዕሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱም መክፈቱን የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አበባ ታመነ ገልፀዋል ።
የሀገራዊ ንቅናቄው ዋና ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል ነው።
እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የሥራ ባህል ማሻሻል ብሎም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ መሆኑን የገለፁት ስራ አስፈፃሚዋ የመገናኛ ብዙኃን ለዘርፉ ስኬት የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑና የዘርፉን የስራ ስኬት ለህዝብ በማሳወቅ እየሰሩት ያለውን ስራ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማስቻል የሚዲያ ፎረም መመስረቱን ተከትሎ በተገባው የስራ ስምምነት መሠረት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ስራ የተመለሱ በአዲስ አበባ እና ሸገር ሲቲ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎችን የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የመጀመሪያ ዙር ጉብኝት እያካሄዱ ነው ።
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙዩኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አበባ ታመነ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የጉብኝቱ አላማ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደስራ የተመለሱ ኢንዱስትሪዎችን የስራ እንቅስቃሴ ለመመልከት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን የጠቀሱት ወ/ሮ አበባ በንቅናቄው በተፈጠሩ ቅንጅታዊ አሰራሮች የዘርፉን ማነቆዎች በመለየት ተዘግተው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት መመለሳቸውን ጠቁመዋል።
ንቅናቄው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶም እስካሁን ከ 600 በላይ ኢንዱስትሪዎች ወደስራ መመለሳቸውን ገልጸዋል።
የሚዲያ ባለሙያዎች የአምራች ኢንዱስትሪ ጉብኝት በቀጣይነት የሚካሄድ መሆኑንም ገልፀዋል።