ሚኒስትሩ በቡራዩ የተገነባውን የፕራይም ቴክ ኢንጅነሪግ የስራ እንቅስቃሴ ጎበኙ

መጋቢት 30/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በቡራዩ የሚገኘውን የፕራይም ቴክ ኢንጅነሪግ ፋብሪካ የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ላይ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ብረቶችንና እንጨቶችን በሚፈለገው ቅርጽ ለመቁረጥ የምንጠቀማቸው ማሽኖች በእጅ የሚሰሩ በመሆናቸው ጉልበትና ጊዜን ይወስዱ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ ይህ ፋብሪካ የሚያመርታቸው የሲኤንሲ ማሽኖች ዓለም የደረሰበትን ከፍተኛ ቴክኖሎጂ የተላበሱና በኮምፒዩተር የሚታገዙ መሆናቸው ስራውን ቀላል፣ ቀልጣፋና ውጤታማ እንደሚያደርገው ገልፀዋል።

ፋብሪካው ገቢ ምርትን በመተካት አስተዋፆው ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ የተወሰኑ ዕቃዎች ከውጪ በማስገባት ምርቶቻቸውን ለማምረት በተለይም ዲዛይን ማውጣት፣ መቁረጥና የመሳሰሉ ስራዎች ተደምረው 75 በመቶ የሚሆኑ ስራዎች በሀገር ውስጥ ግብዓትና በኢትዮጵያዊያን ወጣቶች የሚከናወን ነው ብለዋል።

ለእንጨት፣ ለብረት ስራዎች፣ ለኮንስትራክሽንና ቶርኖ ቤቶች እንዲሁም የተለያዩ ዲዛይኖችን ለመቅረጽ የሚያስችሉ ማሽኖችን እያመረቱ መሆኑ በማምረቻ ኢንዱስትሪዎች የኢትዮጵያዊያንን ፈጠራ ሀሳብና የወደፊት ተስፋ የሚያሳይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ፋብሪካው ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ ታምርት አክስፖ ላይ በመሳተፉ የገበያ ትስስር እንዳገኘ የጠቀሱት ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ምን ዓይነት ተሰጥኦ፣ አቅምና ተስፋ እንዳለ የሚያመላክት ነው ብለዋል ፡፡

መንግስት ወጣቶችን በልዩ ሁኔታ እየደገፈ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርትን የማስፋት ስራ እንደሚሰራ አቶ መላኩ አለበል ገልፀዋል።

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post