አምራች ኢንዱስትሪዉ በቂ ግብዓት እንዲያገኝ የሚያስችሉ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች ተከናውነዋል (አቶ ዳንኤል ኦላኒ)

ሚያዚያ 27/2017 ዓ.ም (ኢሚ) አምራች ኢንዱስትሪዉ በቂ ግብዓት እንዲያገኝ የሚያስችሉ የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች መከናወናቸውን የገለፁት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መሠረተ ልማት እና ግብዓት ዘርፍ አማካሪ አቶ ዳንኤል ኦላኒ የግብርና ምርት ግብዓት በቂ እንዲሆን በኮንትራት ፋርሚንግ አዋጅና መመሪያ መዉጣቱና ወደ ተግባር መግባቱ ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ወደ ውጭ ይላክ የነበረው የብረት ቁርጥራጭ ለሀገር ዉስጥ ግብዓት እንዲሆን መደረጉን፤ ከከፍተኛ አምራቾች ጋር የግብዓት ትስስር እንዲኖር መደረጉ፤ የመጋዘን ደረሰኝ የፋይናንስ ስርዓትን መዘርጋቱ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የስራ ማስኬጃ ካፒታል እንዲያገኙ ከማስቻሉም በላይ ይበልጥ የተረጋጋና ወቅቱን የጠበቀ የግብዓት አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።

የአምራቾች ሀገር ውስጥ የሌሉ የምርት ግብዓቶችን ከውጭ እንዲያስገቡ አስፈላጊው የአሰራር ስርዓት ተዘርግቶ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን የሚጠቅሱት አማካሪው አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከተቀናጁ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች (IAIPs) ጋር የተጠናከረ ግንኙነት እንዲኖራቸው ማድረግ መቻሉ የጋራ መሰረተ ልማትን፣ ቀልጣፋ ሎጂስቲክስን እና ጥራት ያላቸውን ጥሬ እቃዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post