በልማት ባንክ በኩል የተዘረጋው የሊዝ ፋይናንስ ስርዓት ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዕድገት ሚናው የጎላ ነው (ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ )

ሚያዚያ 27/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ 2017 በተለያዩ የሁነቶች ቀጥሏል። በሦስተኛ ቀን ውሎው አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በማብቃት፣ ወደ ዕድገት፣ ተወዳዳሪነት እና ሽግግር ማፋጠን በሚል ርዕሰ ጉዳይ የፖናል ውይይት ተከናውኗል።

በፓናል ውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለባቸው ንጉሴ እንደገለፁት በሀገራችን ያለው በከተሞች ላይ ብቻ የተወሰነ የኢንዱስትሪያላይዜሽን ልምምድ በመቀየር ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሁሉም የገጠር ወረዳ ድረስ ለማስፋፋት የአስተሳሰብ ለውጥ የሚፈጥር የግንዛቤ ማስጨበጫ በስፋት በመስጠት የዘርፉን መሠረት የማስፋት ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።

በተለይም ባለፉት 3 የለውጥ ዓመታት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በፈጠረው መዋቅር በመጠቀም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የስራ ማስኬጃ ብድር ፤ የመስሪያ ቦታ፣ የመሠረተ ልማት እና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በመስጠት ሰፊ ለውጥ ማምጣት ተችሏል።

በተጨማሪም አምራች ኢንተርፕራይዞችን በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን በማጠናከር ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ፣ ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር የድጋፍ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ወደ ስራ መገባቱን ዶ/ር አለባቸው አያይዘው ገልፀዋል።

በዚህ ሁሉ ሂደት አምራች ኢንተርፕራይዞች ዘመኑን የዋጁ ማሽነሪዎችን፣ ቀጣይነት ያለው የንግድ ልማት አገልግሎት እንዲሁም የስራ ማስኬጃ ብድር ተደራሽ ከማድረግ አኳያ በልማት ባንክ በኩል የተዘረጋው የሊዝ ፋይናንስ ስርዓት ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ዕድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል፡፡

በውይይቱም በዋናነት በአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ኦፕሬሽን፣ ምርታማነት እና ፈጠራ የሚያሳድጉ ስትራቴጂዎችን፣ ዋና ዋና ተግዳሮቶች የሚፈቱበትን አቅጣጫዎች፣ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪላይዜሽን ጉዞ ያለውን ሚና ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post