የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ቀልጣፋ የፋይናንስና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ድጋፍ እየተደረገ ነው ፡፡
ሚያዝያ 28/2017(ኢሚ) የአምራች ኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ ቀልጣፋ የፋይናንስና የሎጂስቲክስ አገልግሎት ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዴንጌ ቦሩ ገለጹ።
በሶስተኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ አራተኛ ቀን ውሎ "በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተቋማዊና ቅንጅታዊ አሰራር የአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነትና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ" በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ወቅት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ የጭነት ማጓጓዣ የጊዜና የገንዘብ ወጪ አፈፃጸም ለመቀነስ በተከናወነ የማሻሻያ ተግባር ውጤት እየተመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም ባለፉት አራት ዓመታት በታጁራ ወደብ ብቻ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጨምሮ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ጭነት በማጓጓዝ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን እንደተቻለ አስረድተዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋጋን በመቀነስና አሰራርን በማዘመን ቀጣይነት ባለው መልኩ የአምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍ እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል።
#ኢትዮጵያ_ታምርት
#እኛም_እንሸምት