አምራች ኢንዱስትሪዎችን መደገፍ ምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው ፡፡ (አቶ መላኩ አለበል)

ግንቦት 1/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት፣ ከክልልና ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር የዘርፉን የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በተመለከተ የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው፡፡

የውይይቱን መርሃ ግብር በንግግር የከፈቱት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አምራች ኢንዱስትሪውን መደገፍ ምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትሩ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከማምረት አቅም አጠቃቀምና አዳዲስ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ ከማስገባት አኳያ አበረታች ለውጦች መመዝገብ መቻላቸውን አስረድተዋል ፡፡

የበጀት ዓመቱ የ9 ወራት አፈፃፀማችን ተስፋ ሰጭና የዘርፋችንን ቀጣይ ስኬት በላቀ ደረጃ እውን እንደምናደርግ አመላካች ቢሆንም ከኤክስፖርት አንጻር ገና ብዙ መሰራት ያለባቸው የቤት ስራዎች ስላሉ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ያሉ የዘርፉ አመራሮች ያሉበትን ሁኔታ በጥልቅ ገምግመው የመፍትሄ እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የ2017 ዓ.ም 3ኛው ዙር የኢትዮጵያ ታምርት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ የተያዘለትን ዓላማ ግቡን እንደ መታና ለወደፊት ከዚህ የበለጡ ድንቅ ተግባራትን ለማከናወን የሞራል ስንቅ የተገኘበት ሁነት እንደ ነበር በተሳታፊዎች በተሰጠው ግብረ መልስ ማወቅ ተችሏል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሀገራዊ እልማችንን የምናሳካበት ዋና መሳሪያ እንደ መሆኑ መጠን በመሬት አቅርቦት ችግር፣ በኤሌክትሪክና በሌሎች የምርት ግብዓት ችግሮች ወደ ስራ ያልገቡ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በተመለከተ ሁሉም የዘርፉ አመራር ማነቆዎችን የመፍታት ኃላፊነቱን እንዲወጣ አስገንዝበዋል፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post