በኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪዉ ዘርፉ የኢንቨስትመንት ፍላጎት እየጨመረ ነው(አቶ ሀሰን መሐመድ)

ግንቦት 05/2017 ዓ.ም (ኢሚ) በኬንያ በአፍሪካ አህጉር ነፃ የንግድ ቀጠና የሪል ሶርስ ዋና ኦፕሬቲንግ ከፍተኛ ኦፍሰር ፓትሪክ ንያንግዌሶ በጽ/ቤታቸው ተቀብለው ያነጋገሩት የመሰረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሐመድ የኢትዮጵያ መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ተቀዳሚ የኢኮኖሚ መሰረቱ ለማድረግ አዲስ ፖለሲና የፖሊሲው ማስፈፀሚያ ስትራቴጅዎችን አዘጋጅቶ ወደ ተግባር በመግባቱ ዘርፈ ብዙ ለውጦች እየተዘመገቡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግሮች ቅንጅታዊ በመሆነ አግባብ በመፍታት የዘርፉን እድገት ለማሻሻል የኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ ተቀርፆ እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው በየዓመቱ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ምርታቸውን የሚያስተዋውቁበትና የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት እንዲሁም ከመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር የፊት ለፊት የቀጥታ ምክክር የሚያደርጉበት ኤክስፖ እየተዘጋጀ እምርታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑን አስረድተው ንቅናቄው በፈጠረው መነቃቃት ለሀገር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸውን የዘርፉ ኩባንያዎች ችግር በጥናት ላይ ተመስርቶ የመፍትሔ አቅጣጫ እያስቀመጠ የሚሰራ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ብሩ የሚመራ ብሔራዊ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አብራርተዋል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት 9 ወራት እንደ ሀገር ወደ ስራ ከገቡ 104 የውጭ ኢንቨስትመንቶች /ባለሀብቶች መካከል 74 የሚሆኑት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንደተሰማሩ በመግለጽ አፈፃፀሙ የኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የኢንቨስትመንት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል፡፡

አቶ ሀሰን አክለውም ኬንያዊያን ባለሀብቶችም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በወንድማማችነት መርህ ሁለቱ እህትማማች ሀገራት በጋራ ሰርተው በሚሻሻሉበት ሁኔታን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መዋለ ነዋያቸውን በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ ቢያውሉ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡

በኢንቨስትመንት ኮሚሽን አዘጋጅነት በተካሄደው በ2025 ኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ የምክክር መድረክ ላይ በተገኙበት ወቅት ስለ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ በተደረገ ገለፃ ምክንያት ተነሳሽነታቸውን እንደጨመረ የገለጹት ሚስተር ፓትሪክ ንያንግዌሶ በበኩላቸው ኬንያ ወደ ዓለማቀፍ ገበያው በቀላሉ ለመቀላቀል የሚያስችለውና አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የእድገት መሰረት ለሆነው አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የፋይናንስ አቅርቦት ቀላልና ልዩ ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በቀላሉ ዘርፉን እንዲቀላቀሉ እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ያሳዩ የኬንያ ባለሀብቶች የስራ አዋጭነት ጥናት(የቢዝነስ ፕሮፖዛል )ተዘጋጅቶ ከቀረበ በኋላ ከሁለቱ ሀገራት በኩል የቴክኒክ ኮሚቴ በማቋቋም ስራው ለሁለቱ እህትማማች ሀገራት ያለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በጥልቀት ተገምግሞ ወደ ተግባር የሚገባ ስለመሆኑ ተጠቅሷል።

Share this Post