የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ፕሮፌሰር ላውራንስ ፍሪማን በቢሯቸው ተቀብለው አነጋገሩ

ግንቦት 12/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ተንታኝ ፕሮፌሰር ላውራንስ ፍሪማን በቢሯቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡

የውይይታቸው ዋና ትኩረትም በሀገራዊ ዕድገት በተለይም የአምራች ኢንዱስትሪ አሁናዊ ገጽታ እና በዘርፉ ስላሉ ምቹ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ነበረ፡፡

ዕድገትን ለማምጣት የምንከተለው ፖሊሲ ወሳኝነት አለው ያሉት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ተግባራዊ ያደረግነው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እንደ ሀገር ያሉንን እምቅ አቅሞች አውቀን በየትኞቹ ላይ ማተኮር እንዳለብን ፣ ያለንን ሃብት በማቀናጀት ዕድገትን ማምጣት እንደምንችል እንድንረዳ አስችሎናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የተወሰዱ የማክሮ ኢኮኖሚ እና የንግድና ኢንቨስትመንትና ማሻሻያዎች ለአምራች ኢንዱስትሪው ዕድገት ወሳኝ መሆናቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ከሆኑ ዘርፎች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አንዱ መሆኑና ከፖሊሲ ዝግጅት ጀምሮ አስፈላጊው ማሻሻያ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ዋና ትኩረት ዘላቂና ቀጣይነት ያለው የኢንዱስትሪ ልማትን በማረጋገጥ ሀገራዊ ብልጽግናን ማምጣት ከዘርፉ የሚጠበቅ መሆኑንም አቶ መላኩ ጠቁመዋል፡፡

በውይይታቸውም የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለመደገፍ በመንግስት የተወሰዱ ማሻሻያዎች የድጋፍና ክትትል ስራዎች በዘርፉ የተገኙ ዋና ዋና ስኬቶችና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን አንስተዋል፡፡

የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ተንታኙ ፕሮፌሰር ላውራንስ ፍሪማን በበኩላቸው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሀገር ዕደገት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ዘርፉን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር በሚደረገው ጥረት በጋራ ለመስራት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

Share this Post