በሲዳማ ክልል ለእንስሳት ምርታማነት ተጨማሪ አቅምን የሚፈጥር የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብርካ ተመረቀ
ግንቦት 24/2017 (ኢሚ) በሲዳማ ክልል በሀዋሳ ከተማ በሱፐርኦቫ አግሮቴክ ኃ.ተ.ግ.ድ የተገነባ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተመርቆ በይፋ አገለልግሎት መስጠት ጀምሯል ።
ፋብሪካው ከዚህ በፊት ከነበሩት ሠራተኞች በተጨማሪ ከ100 በላይ ወጣቶች የስራ ዕድልን እንደሚፈጥር ተገልጿል።
የሲዳማ ክልል ም/ርዕሰ መስተደድርና የት/ት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ ባራሳ ፋብሪካው ለክልሉ ማህበረሰብ ተጨማሪ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑና በ2018 በጀት ዓመት ከ20ሚሊዮን በላይ ዶሮዎችን ለማሰራጨት ስለታቀደ መልካም አጋጣሚ መሆኑንና ህብረተሰቡ ይህን ዕድል በመጠቀም ምርታቸዉን በስፋት አምርተዉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስተር የመሰረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ ሚንስቴር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ እንደገለፁት የሲዳማ ክልል መንግስት ልዩ ትኩረት በመስጠቱ በኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕድገት እየታየ መሆኑን ገልፀዉ ፣ ፋብሪካዉ የክልሉን ብቻ ሳይሆን የሀገርቱን የሌማት ትሩፋት ዕቅድን ለማሳካት እንደሚረዳና ሚኒስተር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጎሳየ ጎዳና በበኩላቸው በሲዳማ ክልል ከ1300 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች መኖራቸዉንና ሌሎች በየትኛውም ዘርፍ እንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ ልማታዊ ባለሀብቶች ሁሉ ክፍት መሆኑንና የክልሉ መንግስትም አስፈላጊዉን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የፋብሪካዉ መስራችና ባለቤት ኦፊር ሌቪ እንደገለፁት ይህ ፋብሪካ የእንስሳትን መኖ በማቀነባበር የእንስሳት ምርታማነትን በመጨመር የህብረተሰቡን የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ ጉልህ ሚና እንዳለሁ ገልፀው ፋብሪካዉ በሰዓት 15 ቶን እንደሚያመርትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም አከባቢዎች ምርቱን እንደሚያደርሱም አስረድተዋል።
#ኢትዮጵያ_ታምርት
#እኛም_እንሸምት