የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የክልሉ ኢንቨስትመንት ፍሰትን እንዲነቃቃ አድርጓል(ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ)
ግንቦት 26/2017(ኢሚ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ፍሰትን የበለጠ እንዲነቃቃ ማድረጉን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ተናገሩ።
በክልሉ የኢንቨስትመንት ፍሰት በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በብዛትም ሆነ በጥራት እየተሻሻለ መጥቷል ብለዋል።
ንቅናቄው የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በቅርበት እንዲሰሩና በዘርፉ ያለው ማነቆ እንዲፈታ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም መንግስት፣ ባለሃብቱ፣ የፋይንስ ተቋማት በቅንጅት በመስራት ዘርፉ እንዲነቃቃና እንዲተዋወቅ አስችሏል ብለዋል።
የሥራ እድል ፈጠራ እንዲጨምር፣ ለወጪ ንግድ የሚሆኑ ምርቶችን በስፋት እንዲመረቱ ማስቻሉን ጠቁመው፤ የክልሉ መንግስት በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በዚህም የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻልና ቀልጣፋ በማድረግ ተወዳዳሪ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመገንባት በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የክልሉ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ እንድሪስ አብዱ በበኩላቸው ቢሮው ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በክልሉ ባለሀብቶች በስፋት እንዲሰማሩ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ልማት ለአገር እድገት መሰረት መሆኑን ያነሱት ሃላፊው፤ የመሬት አቅርቦት፣ የሃይል፣ የብድር እና ሌሎች የዘርፉን ግብአቶች በስፋት ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በክልሉ የኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግም በትኩረት መሰራቱን ተናግረዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው በበኩላቸው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጎንደርን በአዲስ መልክ ወደ አምራችነት በመመለስ ረገድ ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩን ገልጸዋል።
በከተማዋ የተጀመረው ኢንዱስትሪ ልማት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በጎንደር አካባቢ ያሉ የተፈጥሮ ሃብቶች ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ግብአትነት ትልቅ አቅም መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ከተማዋ በቀጣይ በርካታ ባለሃብቶችን ተቀብላ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗንና ኢንቨስትሮች በስፋት ወደ ከተማዋ ገብተው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።