የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ የወደፊት እጣ ፈንታ በመቅረጽ ረገድ የቋሚ ኮሚቴው ሚና የላቀ ነው ( አቶ ሀሰን መሃመድ )
ሰኔ 09/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለኢንዱስትሪና ማዕድን ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት በአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ የማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት እያካሄደ ነው።
በሚኒስቴሩ የመሠረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ሀሰን መሃመድ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ የሀገራችንን የኢንዱስትሪ ዕድገት እና ሽግግር የሚያፋጥኑ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ግንዛቤ በመፍጠር እየተደረገ ያለውን ዘርፈ ብዙ ድጋፍ፣ ትኩረትና ክትትል ውጤታማ በሆነ መንገድ ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግን ታሳቢ አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል ።
የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ የወደፊት እጣ ፈንታ በመቅረጽ ረገድ የቋሚ ኮሚቴው ሚና የላቀ ነው ያሉት አቶ ሀሰን የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቱ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰው ሃብት ልማት ስትራቴጂ፣ የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ሞዴል፣ የቆዳ ስትራቴጂ፣ የኤክስፖርት እና ተኪ ምርት ስትራቴጂ ላይ ለድጋፍና ክትትል ስራችን በሚያግዝ መልኩ ጥልቅ ውይይት ይደረጋል ብለዋል።
ለኢትዮጵያ የበለጸገ አምራች የኢንዱስትሪ ዘርፍ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ቋሚ ኮሚቴው እየሰጠ ላለው ትኩረትና ቁርጠኝነት ትልቅ አድናቆት እንዳላቸው በመግለፅ ቋሚ ኮሚቴው ድጋፍና ክትትሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል ።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዶክተር አማረች በካሎ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን በመደገፍ ዘርፉ ለሀገር ዕድገት ያለውን አበርክቶ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ የሚያደርግ ድጋፍ ለማድረግ ፖሊሲውንና ማስፈፀሚያ ስትራቴጅዎች ላይ ግንዛቤ መያዝና መግባባት ላይ መድረስ ተቀዳሚ ስራ መሆኑን በመጠቆም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኢንሸቲቭ እየተተገበሩ ያሉ እንደ ገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ያሉ ስራዎች በተጨባጭ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተግባራዊ ከተደረጉ ኢትዮጵያ የያዘችው የብልግፅና ጉዞ እውን እንደሚሆን ዋና ማረጋገጫ ነው ብለዋል።
#ኢትዮጵያ_ታምርት
#እኛም_እንሸምት