የኢንዱስትሪ ከፍተኛ አመራሮች ቢሸፍቱ ከተማ የሚገኙ አምራች ኢዱስትሪዎችን ጎበኙ።

ሰኔ13/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ፤የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ፣ የቢሸፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ እንዲሁም የኦሮሚያ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊዎች እና የክልሉ የስራ ኃላፊዎች በከተማዋ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ጉበኙ፡፡

ጉብኝቱ አምራች ኢንዱስትሪዎቹ ያሉበትን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴዎቻቸው ምን እንደሚመስል፣ በስራ ላይ ያጋጠማቸውን ችግሮች በመፈተሽ የመፍትሔ አቅጣጫ ለመስጠትና እና ድጋፍ ለማድረግ ዓለማ ያደረገ ነው ፡፡

ኤን ኤች ቢ (NHB) የቤት እና የቢሮ ዕቃዎች ፋብሪካ ፤ ኪያ የውሃ ማምረቻ ፋብሪካ እና ጂኤስ ብረታ ብረት ፋብሪካ በተደረገው የመስክ ምልከታ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እና የማምረት አቅማቸውም ከፍተኛ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡

በዋናነት መንግስት እየተከተለ ባለው ኤክስፖርትን ማበረታታት ፣ ገቢ ምርት መተካት፣ ለዜጎች የስራ እድል መፍጠር ፣ የማምረት አጠቃቀም ማሳደግ ስራ አምራች ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ ስራዎች እየሰሩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል በግንባታ ላይ ያሉ ባንቦ ወረቀት ፋብሪካ እና ቲኤችጂ (THG) የታሸጉ ካርቶኖች እና የህትመት ውጤቶች ፋብሪካ የመስክ ጉብኝት የተደረገ ሲሆን ያሉበት የግንባታ አፈፃፀም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለ ለመረዳት ተችሏል ፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታውን አጠናቀው ወደ ምርት ስራ ውስጥ እንደሚገቡ ከተቋሙ ኃላፊዎች የተገለጸ ሲሆን ወረቀት ፋብራካዎች ወደ ስራ ሲገቡ የሃገር ውስጥ የወረቀት ፍጆታን በመሸፈን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያድን ይገመታል ፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን በመደገፍ እና ችግሮችን በመፍታት ተወዳዳሪ ለማድረግ መንግስት ከፋይናንስ ተቋማት፣ ከሎጀስቲክ ፣ ከገበያና ግብዓት ትስስር እንዲሁም ከመሰረተ ልማት ጋር በተያየዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በልዩ ትኩረት በቅንጅት እየሰራ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post