በአምራች ኢንዱስትሪዎቻችን አማራጭ ሀይል መጠቀም በመቻላችን ከሶስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ከብክነት ማዳን ችለናል(አቶ ሀሰን መሀመድ)

ሰኔ 21/2017 ዓ.ም(ኢ/ሚ)የኢፌድሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ አረምን እንደ ሀይል አማራጭነት መጠቀምን አስመልክቶ በተሰሩ ስራዎች ዙሪያ የልምድ ልውውጥ ሰሚናር አካሄደ፡፡

ድሬደዋ ከተማ ተገኝተው በመርሀ ግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመሠረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ ፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራን እንደ አማራጭ ሀይል መጠቀማችን ቀደም ሲል ለስሚንቶ ፋብሪካዎች የድንጋይ ከሰል ከውጭ ለማስገባት ይወጣ የነበረን ከሶስት ሚሊዮን በላይቤሪያ ዶላር ከብክነት ማዳን ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አረሙ በአርብቶ አደሮች አካባቢ የሚሰጠው አንዳንድ ጥቅሞች ቢኖሩም በሌላ በኩል ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው ያሉት አቶ ሀሰን እስካሁን የተገኙ መልካም ውጤቶችን በማስቀጠል በፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ አረም ላይ እየተሰራ ያለውን ፕሮጀክት ዋና ዓላማ መቶ በመቶ ለማሳካት የግሉ ዘርፍ ሚና ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለውጥ ሴክተር ሪፎርም ፐርፎርማንስ ፐሮጀክት የፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ አረምን ከስጋትነት ወደ ኢንዱስትሪ ግብዓትነት ለመቀየር የተደረገውን ጥረት በመሐል ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ መጥፎ ክስተቶች ቢፈትኑትም አሁን ላይ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ራሱን የቻለ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

በነበረው መርሀ ግብር በፕሮጀክቱ የአሰራር ሂደት የነበሩ ተሞክሮዎችን አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲቀያየሩ ከማድረግ ባሻገር ለፕሮጀክቱ ስኬት የጎላ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት ዕውቅናና ሰርተፍኬት ተሰጥቷል፡

በመጨረሻም ማንኛውንም ተግዳሮት ወደ መልካም ዕድል መቀየር እንደሚቻል ከዚህ ፕሮጀክት ትምህርት በመውሰድ የዘርፉ ባላድርሻ አካላት ለላቀ ውጤት መትጋት እንዳለባቸው በሚኒስትር ደኤታው አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡

በሰሚናሩ የስሚንቶ ፋብሪካ ተወካዮች፣የዩኒቨርስቲ ምሁራንና የሚመለከታቸው አመራር ሰጭ አካላት ተሳትፈውበታል፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post