የድንጋይ ከሰልን በባዮ ማስ መተካት በመቻላችን እጅግ በጣም ተጠቃሚ ሆነናል(የክብር ዶ/ር ብዙአየሁ ታደለ)
ሰኔ 23/2017 ዓ.ም (ኢ/ሚ) የናሽናል ስሚንቶ ፋብሪካ ባለሀብት የክብር ዶ/ር ብዙአየሁ ታደለ ቀደም ሲል ለፋብሪካቸው በግብአትነት ሲጠቀሙት የነበረውን የድንጋይ ከሰል በፕሮሶፒስ ጁሊፍሎራ ባዮ ማስ መተካት በመቻላቸው ተጠቃሚ እንደሆኑ ገልጸዋል ፡፡
የአማራጭ ሀይልን መጠቀም አስመልክቶ በአፍሪካ ስሚንቶ ምርት ግንባር ቀደም ወደ ሆነችው ግብጽ ሀገር ሄደው ተሞክሮ መቅሰማቸውን የተናገሩት ባለሃብቱ በኢትዮጵያ የአማራጭ ሀይል አጠቃቀምን ለማስረጽ ለመጀመሪያ ጊዜ የድርሻቸውን ለመወጣት ቢሮ ከፍተው በመስራት ረገድ የመጀመሪያው ሰው እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እጅግ በጣም አዋጭ ፕሮጀክት ቀርጾ በሰራው ስራ የድንጋይ ከሰልን በባዮ ማስ ተክተን እንደ አንድ የሀይል አማራጭ መጠቀም መቻላቸውን ያብራሩት የክብር ዶ/ር ብዙአየሁ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለሰጣቸው ዕውቅናና ሰርተፍኬት ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
መንግስት የዘርፉ ባለሀብቶችን ለማበረታታት እየሰራ ያለው ስራም ለሌሎች ስራ ፈጣሪ ባለሀብቶች ከፍተኛ የሞራል ስንቅ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
#ኢትዮጵያ_ታምርት
#እኛም_እንሸምት