አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ገፅታ በመቀየር እየተከልን ኢትዮጵያ እንድታንሰራራ ማድረግ አለብን የሚል ነው (አቶ መላኩ አለበል)

ሐምሌ 10/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ስራ የተፈጥሮ ሚዛንን ከመጠበቅ ባለፈ ማህበራዊ ግንኙነትን በማጠናከር አካላዊና አዕምሯዊ ጤናን በማስተካከል ሚናው ከፍተኛ ነው ያሉት ሚኒስትሩ አቶ መላኩ እንደ ሀገር በ2017 ዓ.ም የክረምት ወቅት 7.5 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል በእቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን በመጥቀስ እቅዱን ለማሳካት በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ በእቅድ ከተያዘው በላይ እንደሚሆን እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አመላካች ናቸው ብለዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት አመራርና ሠራተኞቻቸው ጋር በጋራ"በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው እለት በቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግቢ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል፡፡።

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለፁት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋንን በማሳደግና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ከመሆኑም ባሻገር የወጪ ንግድ ምርቶችን በአይነትና በጥራት በማምረት ለውጪ ምንዛሬ ግኝት እድገት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በተሰራ አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የተተከለው የቡና ችግኝ በያዝነው በጀት ዓመት በቡና ኤክስፖርት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ስለመቻሉ ገልጸዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን በመትከል የአካባቢ ስነ-ምህዳርን በማስተካከል የአካባቢ ጥበቃ ስራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡

የተሳለጠ የንግድ ስርዓት እንዲፈጠር የራሳችን የምንሸጠውና የምንገዛው ምርት ሊኖረን ያስፈልጋል በመሆኑም የምንሸጠውና የምንገዛው ነገር እንዲኖረን የምናመርተው ምርት ሊኖረን ግድ እንደሆነ በመገንዘብ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርትና ምርታማነት ሂደት ሊያቀላጥፉ የሚችሉ የአሰራር ስርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግና በመደገፍ የምናመርታቸው ጥሬ ሀብቶቻችን እሴት የተጨመረባቸውና በዓለም ገበያ ተፈላጊነት ያላቸው ምርቶችን በማምረት መግዛትና መሸጥ ይኖርብናል ብለዋል፡፡

ለትውልድ በጎ ተግባርና እሴትን ለማውረስ የአረንጓዴ አሻራ ስራ አንዱ ማሳያ መሆኑን የገለጹት አቶ መላኩ አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ገፅታ በመቀየር በኩል እየተከልን ኢትዮጵያ እንድታንሰራራ ማድረግ አለብን የሚል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም የ2018 በጀት ዓመት እቅድን ለማሳካት ሁሉም የበኩሉን አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዲያበረክት አሳስበዋል፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post