ሀገር በቀል አምራች ኢንዱስትሪዎች ሊበረታቱ ይገባል (አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ)

ሀምሌ17/2017 ዓ.ም (ኢ.ሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትና ዕድገት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰማሩ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን የማበረታታት ስራዎች በትኩረት እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡

አቶ ታረቀኝ ለቴክኖሎጅ ሽግግር ያመች ዘንድ በዘርፉ የሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶችን መሳብና ማሰማራቱ ጥሩ ቢሆንም በሀገር ውስጥ ያሉ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለሀብቶችንም የሀገር ባለቤት መሆናቸውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በትኩረት መከታተልና መደገፍ የዘርፉን ዕድገት በዘላቂነት እንደሚያስቀጥል አብራርተዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው ያሉት አቶ ታረቀኝ ለዘርፉ ብቁና የሰለጠነ የሰው ሀይል ከማቅረብ አኳያ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ከሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ጋር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በጥምረት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ስራ እንደ ሀገር አዲስ የኢንዱስትሪ ማህበረሰብ ከመፍጠር አንፃር ፋይዳው የጎላ ስለሆነ ፈፃሚው ከሚተገብራቸው ዋና ተግባራት ጋር ደርቦ በትጋት መስራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

አክለውም ለ2018 በጀት ዓመት የታቀደው ተቋማዊ ዕቅድ የሁሉም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመራርና ሰራተኛ ንቁ ተሳትፎና ርብርብ የሚሳካ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዕቅዱ መሳካት ሁሉም የራሱን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post