አሁን ላይ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ እየታዩ ያሉ መሻሻሎችን በዘላቂነት ማስቀጠል ይገባል (አቶ መላኩ አለበል)

ሀምሌ17/2017 ዓ.ም (ኢ.ሚ) የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል አሁን ላይ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከማምረት አቅም አጠቃቀምና ከኤክስፖርት አኳያ ያሉ መሻሻሎችን በዘላቂነት ማስቀጠል እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ባመጣው አዎንታዊ ለውጥ ቀደም ሲል አምራች ኢንዱስትሪዎች የነበረባቸውን የገበያ ችግር መቅረፍ ማቻሉን የገለጹት አቶ መላኩ የዘርፉን ችግር ለመፍታት ከቅንጅታዊ አሰራር አኳያም ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በተሰራው ስራ አበረታች ለውጥ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በ2017 በጀት ዓመት የተጀመረው የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽን ንቅናቄ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲገቡ ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡

አክለውም በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡት ውጤቶች ሊመጡ የቻሉት የነበሩ ችግሮችን በጥልቀት መረዳትና መለየት በመቻሉ ስለሆነ ምንግዜም ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ድጋፎች ሲደረጉ ያሉባቸውን ችግሮች በቅድሚያ ለይቶ በማቀድ እንጅ በዘፈቀደ መሆን እንደሌለበት አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም በ2018 በጀት ዓመት ሁሉም ባለድርሻ አካል የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጅዎችን ተግባራዊ ማድረግ፣ ከሌሎች ተግባራት እኩል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ መስራት፣ ኤክስፖርትን ለማሳደግ መጣር፣ የብሔራዊ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል ውሳኔዎችን ተከታትሎ ማስፈፀም፣ ለየት ያለ አካሄድ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች የመለየት ስራ መስራትና ለሞጆ ሌዘር ሲቲ ምስረታ መሳካት ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post