የመግባቢያ ሰነዱ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የኃይል አጠቃቃም ለማሻሻል የሚረዳ እና በጋራ መስራት የሚያስችል ነው። (አቶ ሃሰን ሙሐመድ)
ነሀሴ 7/2017 ዓ.ም (ኢ.ሚ) የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እና የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የሃይል አጠቃቀም ለማሻሻል የሚያስችላቸውን የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ፡፡
የሰነዱ ዋና ዓላማ ተቋማቱ የተቋቋሙበትን ዓላማ በማቀናጀት ፣ እውቀትን በማካፈልና ሃብት በማቀናጀት፣ ለዘላቂ የኢንዱስትሪ እድገት ምቹ የሆነ አካባቢ ለመፍጠር መሆኑን በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማትና ግብአት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሃሰን መሃመድ ገልጸዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የወደፊቷ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ከመሆኑም በዘለለ የሀገራችን ዘላቂ ልማት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ያሉት አቶ ሃሰን ዘርፉ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲያድግ፣ በአከባቢ እና ተፈጥሮ ሃብት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽኖ እንዲቀንስ ፣ እንዲሁም ዘርፉ ለሀገራችን ብልፅግና እንዲረዳ የማድረግ ሃላፊነት ከምንጊዜውም በላይ የሚያስፈልግበት ወቅት በመሆኑ የመግባቢያ ሰነዱ ማስፈለጉን ገልጸዋል፡፡
ከ20 እስከ 30 በመቶ የሃይል ብክነት እንዳለ በተለያዩ ጊዜያት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተደረጉ የሃይል አጠቃቀም ጥናቶች ያመላክታሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ለዚህም የግንዛቤ እና የአመለካከት ችግሮች፣ በኢንዱስትሪዎች የሃይል አስተዳደር ስርዓት ያለመኖር፣ ጊዜ ያለፈባቸው ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ ቴክኖሎጂዎች በስፋት ስራ ላይ ያሉ መሆናቸው እና የአቅርቦት ጥራት ችግሮች በመንስኤነት እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል፡፡
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአየር ንብረት ለውጥ ሴክትረ ሪፎርም ፐርፎርማንስ ፕሮጀክት አማካኝነት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ብቃት ያለው እና ከብክነት የጸዳ የሃይል አጠቃቀም ስርዓት እንዲኖር በተደረጉ ተከታታይ የአቅም ግንባታ፤ የምርምር እና የኢነርጂ ኦዲት ስራዎች በዘርፉ የተሻለ ግንዛቤ መፍጠር መቻሉንም ሚኒስትር ዴኤታው አክለዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪዎቻችን ኃይልን በብቃት እንዲጠቀሙ እና የታዳሽ የኃይል አማራጮችን ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ከማድረጉም ባሻገር የተፈጥሮ ሃብት ብክነትን፤ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ እና ለመጪው ትውልድ ይበልጥ አረንጓዴ የሆነ የወደፊት ሕይወት እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደርጋል ያሉት አቶ ሃሰን ለዚህም ቀጣይነት ባለው መልኩ በጋራ እንሰራለን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
#ኢትዮጵያ_ታምርት
#እኛም_እንሸምት