በኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ዕድገት ዘላቂ እና አካታች እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ነሐሴ 14/2017 ዓ.ም (ኢሚ) ኢትዮጵያ ባቀረበችው የአየር ንብረት ኢንቨስትመንት ፈንድ የኢንዱስትሪ ዲካርቦናይዜሽን (Climate Investment Fund Industrial Decarbonization) ፕሮግራም ውይይት ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ መሰረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ተጋላጭ ላለመሆን በአርንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ጠንክራ እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል ።

የClimate Investment Fund Industrial Decarbonization ፕሮግራም ተጠቃሚ ለመሆን ያላትን ጠንካራ ፍላጎት ያሳየችው በዚህ ግንዛቤ እና የማያወላውል ቁርጠኝነት ነው ብለዋል።

ጠንካራ የሆነ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ኢትዮጵያን ለውጭ ኢንቨስትመንት ማራኪ መዳረሻ እንደሚያረጋት የገለፁት አቶ ሀሰን መሀመድ ከአጋር አላካት የሚገኝ የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፍ ቴክኖሎጂን ለማዘመን፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ፈጠራ፣ ጠቃሚ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ እና ለዜጎቻችን በተለይም ለሴቶችና ለወጣቶች በጣም አስፈላጊ የሆኑ አረንጓዴ የስራ ዕድሎችን መፍጠር እንደሚያስችል ገልፀዋል ።

ከአጋር አካላት የሚገኘው ድጋፍ በአምራች ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለውን የእሴት ሰንሰልት በማቀላጠፍ ከዘርፉ የሚመነጨውን ቆሻሻ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል ያሉት አቶ ሀሰን መሀመድ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ማህበረሰብን ግንዛቤ በማሳደግ እና በንግዱ ማህበረሰብ እና በአጠቃላይ ህዝብ መካከል ያለውን ተሳትፎ ለማጎልበት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

በዘረፉ የሚመለከታቸው አካላት መንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች፣ ዓለም አቀፍ አጋሮች እና ሲቪል ማኅበረሰቦች አረንጓዴ እና በአለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለመፍጠር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

#ኢትዮጵያ_ታምርት

#እኛም_እንሸምት

Share this Post