በቀሪው አምስት አመታት የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም አጠቃቀም ዕቅድ ለማሳካት ቅንጅታዊ አሰራሮች ወሳኝነት አላቸው። (ዶ/ር አያና ዘውዴ )
ነሐሴ 15/2017 ዓ.ም (ኢሚ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተግባራዊ ከተደረገ 2014 በጀት አመት ጀምሮ በርካታ ውጤቶች መጥተዋል ያሉት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፕሮጀት ጽ/ቤት አስተባባሪ አያና ዘውዴ (ዶ/ር) ይህም የቅንጅታዊ አሰራር መጠናከር ውጤት መሆኑን ገልፀዋል።
ንቅናቄው ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ የተግባር እና ባለቤትነት መፍጠር በሚሉ ሶስት ምዕራፎች የተከፈለ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው በተለይም የመጀመሪያ የሆነው የግንዛቤ ማስጨበጭ ምዕራፍ በባለድርሻ እና ሚዲያ አካላት ቅንጅት አስፈላጊው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ የተሰራበት እና ውጤታማ እንደነበር ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሲጀመር መሰረታዊ አላማው መዋቅራዊ ችግሮችን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ብቻ መፍታት ስለማይችል የተባባረና የተቀናጀ እንዲሁም ተቋማዊ የሆነ በዕቅድ የሚመራ አደረጃጀት ተፈጥሮ መዋቅራዊ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ርብርብ ተደርጓል ብለዋል።
በተጫማሪም አስፈላጊውን አደረጃጃት በመፍጠር ከግብዓት፣ መሰረተ ልማት፣ በቂ የሰው ኃይል ከማቅረብ ፣ የፋይናስና መንግስታዊ አገልግሎቶችን በማሻሻል የዘርፉን ችግሮች ደረጃ በደረጃ እየቀረፍን መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት ተችሏል።
አደረጃጀቱን የሚደግፍ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል ተቋቁሞ አስፋላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት ዶክተር አያና በዘርፉ ከመጡ ለውጦች በማሳያነት የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም 65 በመቶ መድረሱን በማንሳት ቀሪው 20 በመቶ በቀጣይ አምስት አመታት ውስጥ መሳካት እንዳለበትና ለዚህም ከፌደራል ጀምሮ በሁሉም የኢትዮጵያ ታምርት አደረጃጀቶች አስፈላጊውን ስራ በመስራትና ግልፅ ዕቅድ በማዘጋጀት እንዲሁም ለዕቅዶቹ መሳካት ከዚህ በላቀ ቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
#ኢትዮጵያ_ታምርት
#እኛም_እንሸምት