የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ልማት አጀንዳ ጋር ሙሉ በሙሉ የተጣጣሙ ናቸው
መስከረም 21/2018 ዓ.ም (ኢሚ) በጣሊያ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (AICS) የሚደገፈው የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ፕሮጀክት ኦፕሬሽንና ዘላቂነት ሶስተኛው የፌዴራል የፕሮጀክት አስተባባሪ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመሰረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሃመድ እንደገለፁት ይህ ፕሮግራም የፖሊሲ መለኪያ ብቻ ሳይሆን ግብርናን ከኢንዱስትሪ ጋር ለማስተሳሰር፣ የግብርና ፕሮሰሲንግ ዘርፉን ለማጠናከር እና ለአርሶ አደሩና ለሥራ ፈጣሪዎች ሁሉን አቀፍ ዕድሎችን ለመፍጠር የተነደፈ መሆኑን ገልፀዋል ።
የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የረጅም ጊዜ ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማጎልበት፣ ከህብረት ስራ ማህበራት ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር እና ለጥቃቅንና አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ጠንካራ ድጋፍ ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል ።
የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ልማት አጀንዳ ጋር ሙሉ በሙሉ የተጣጣሙ ናቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ፓርኮቹ የምግብ እሴት ሰንሰለቶችን በማዋሃድ፣ በድህረ ምርት የሚደርሰውን ኪሳራ በመቀነስ፣ የትራንስፖርት ወጪን በመቀነስ፣ የኢነርጂ ቆጣቢነትን በማሻሻል ፣ በተሻሻለ የምርት ጥራት ምርታማነት ለማሳደግ የተነደፋ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ከ16,000 በላይ ዜጎች የስራ ዕድል የተፈጠረ ሲሆን ከ274,000 በላይ አነስተኛ አርሶ አደሮች መሰማራታቸውን አስረድተዋል።
የጣልያ የልማት ትብብር (AICS) የኢትዮጵያን የግብርና ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን በማስተዋወቅ ላደረገው ቅን አጋርነት የኢትዮጵያ መንግስት ያለውን ልባዊ ምስጋና አቀርባለሁ ያሉት አቶ ሀሰን መሀመድ ለዚህ ሦስተኛው የፌዴራል የፕሮጀክት አስተባባሪ ኮሚቴ ስብሰባ በተገኘው ውጤት፣ ተግዳሮቶች እና በተገኙ ትምህርቶች ላይ ግልጽ፣ ገንቢ ውይይቶችን በማድረግ ባደረጋችሁት ቁርጠኝነት እና አስተዋፅዖ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉን አቀፍ እና ቀጣይነት ያለው የአግሮ-ኢንዱስትሪ ልማት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል።