የግል ዘርፉን ምርታማነት፣ ኢንቨስትመንት እና ኤክስፖርትን ማሳደግ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ
መስከረም 20/2018 ዓ.ም ( ኢሚ) የአፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ከአለም ባንክ ቡድን የኢትዮጵያ ጽ/ቤት (World Bank group-Ethiopia country office) ተወካዮች ጋር የጋራ ትብብራቸውን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ ፡፡
በውይይቱ ለኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ልማት የዓለም ባንክ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች እና ባንኩ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ያሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከማሳ (እርሻ) እስከ ገበያ ባለው ሂደት የሚገጥማቸውን ተግዳሮቶች መነሻ በማድረግ ውይይት የተካሄደ ሲሆን በዚህም በተመረጡ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ የግሉ ዘርፍ ምርታማነትን፣ ኢንቨስትመንትን እና ኤክስፖርትን ማሳደግ ላይ ትኩረት አድረገው ለመስራት እቅዱ ያላቸው መሆኑ በአለም ባንክ ቡድን የኢትዮጵያ ጽ/ቤት ተወካይ ልዑካን ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን የድጋፍና ክትትል ሰራዎች በማስፋት ፣ ከውጪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት እና የውጪ ምንዛሬ ገቢን በማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪውን ውጤታማነት ለማሳደግና በተለያዩ ደረጃዎች እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ያመላከቱት አቶ መላኩ ባንኩ እስካሁን እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባና በተነሱ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንሰራለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በአለም ባንክ ቡድን የኢትዮጵያ ጽ/ቤት ተወካይ ዳይሬክተር መርየም ሳሊም የተመራው ልዑክ ባንኩ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር ያለውን ትብብር ለማስቀጠል የአምራች ኢንዱስሪዎችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡