የግብርና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት የማዕዘን ድንጋይ ነው።

መስከረም 21/2018 ዓ.ም (ኢሚ) በጣሊያ የልማት ትብብር ኤጀንሲ (AICS) የሚደገፈው የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ፕሮጀክት ኦፕሬሽንና ዘላቂነት ሶስተኛው የፌዴራል የፕሮጀክት አስተባባሪ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ (AICS) ኃላፊ ዶክተር ሚሼል ሞራና የጣሊያን ትብብር ከኢትዮጵያ ተቋማት ጋር ጠንካራ እና ውጤታማ አጋርነትን መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልፀዋል ።

የግብርና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች የስራ እድሎችን ለመፍጠር እና የግብርና ምርቶችን ጥራት እና ምርታማነት ለማሳደግ ትኩረት አድርገው መጀመራቸውን ጠቁመዋል ።

የጣሊያን ትብብር የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዓላማ መሠረት በማድረግ ኢንቨስትመንት የመነሻ ጥናቶችን፣ የምህንድስና እና የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማዎችን እና የእሴት ሰንሰለት ትንተናዎችን ጨምሮ የተለያዩ ወሳኝ እንቅስቃሴዎችን መደገፋን አስረድተዋል ።

በሁለቱ ሀገራት ኢንተርፕራይዞች መካከል ተጨማሪ የንግድ ለንግድ ትብብርን ለመደገፍ እና ለማበረታታት ዝግጁ ነን ያሉት ዶክተር ሚሼል ሞራና የግብርና-ኢንዱስትሪ ልማት እና ለሁለቱም ሀገራት ኢኮኖሚ ዘላቂ ጥቅሞችን ለማስገኘት በጋራ መስራት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል ።

ቀጣይነት ያለው ድጋፍ የኢትዮጵያን የግብርና ምርቶች ጥራት እና የተጨመረ እሴትን በማረጋገጥ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነታቸውን ማሳደግ እንደምንችል በፅኑ አምናለሁ ብለዋል።

Share this Post