የግል ዘርፉን የማደራጀት አስፈላጊነቱ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን እምቅ ሃብት በተደራጀ አግባብ ለመጠቀምና መምራት ለማስቻል ነው (ወ/ሪት ካሳዬ ዋሴ)
መስከረም 24/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪው እድገትና ተወዳዳሪነት ማደግ ላይ ያለውን የማይተካ ሚና ለማጎልበትና ከመንግስት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር ከግል ዘርፍ ማህበራት አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ የቀጣይ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በውይይት መድረኩ ከለውጡ አመታት ወዲህ በብዝሃ ዘርፍ የኢኮኖሚ እድገት አማራጭ ትኩረት ከተሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች አንዱ የሆነው የእምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን እድገት ለማምጣት የተሰሩ ስራዎች፣የተገኙ ውጤቶችና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ሰነድ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስትራቴጂክ ጉዳዮች ስራ አስፈፃሚ በኩል ቀርበዋል።
በሌላ በኩልም የእለቱን አጀንዳ አስመልክቶ የግል ዘርፍ ማህብራት አስፈላጊነት፣ እንደ ሀገር ያሉበት ደረጃ ፣ የታዩ ክፍተቶችና የቀጣይ አቅጣጫዎን የሚያመላክት የመነሻ ሰነድ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴረር የብቃትና ፈቃድ አገልግሎት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ካሳዬ ዋሴ ቀርቧል።
የግሉን ዘርፍ ማደራጀት አስፈላጊ የሆነበት ዋና አላማ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለውን እምቅ ሃብት ከፌደራል እስከ ክልልና ከተማ አስተዳደር በተደራጀ አግባብ ለመጠቀምና መምራት ለማስቻል መሆኑን ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አመላክተዋል።
የግል የዘርፍ ማህበራት መጠናከር ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ፣በራስ አቅም ሃብትን በማመንጨት ድጋፍ የሚያደርጉበትን አግባብ ለማስቀጠልና በሀገር ውስጥና በአለም አቀፍ መድረኮች ዘርፉ የሚተዋወቅበትን የመልማትና መስፋፋት ሂደቶች በተደራጀ አግባብ የሚያስተዋውቁበን መንገድ ለመፍጠር ነው ሲሉ ያከሉት ስራ አስፈፃሚዋ በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ማህበራቶች አቅማቸውን በማጎልበት ከመንግስት ጋር በጥምረት ሊሰሩ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በሶስተኛነት ደረጃም የተመረጡ የግል ማህበራት ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳዩ ሰነዶች ያቀረቡ ሲሆን ሰነዶችን ተከትሎ ውይይት ተካሂዷል።
ውይይቱን ተከትሎም የግል ዘርፍ ማህበራትን የማጠናከር፣ ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር የተናበበ የ5 አመት ስትራቴጂክ እና አመታዊ እቅድ እንዲያዘጋጁ፣ ከመንግስት ጋር የሚወያዩበት አመታዊ የጊዜ ሰሌዳ የማስቀመጥ እንዲሁም በግል ዘርፉ እና በመንግስት በኩል መፈታት የሚገባቸውን ችግሮች ተለይቶ ችግሮቹን በባለቤትንት የሚፈቱበት አግባብ አንዲፈጠር እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ስራዎች ላይ የጋራ አቅጣጫ በማስቀመጥ ውይይቱ ተጠናቋል።