የፖሊሲ ማስፈጻሚያ ስትራቴጂዎች የታለመውን ለውጥ እያመጡ ይገኛል (ዶ/ር ገመቹ ጌታሁን )
መስከረም 30/2018 ዓ.ም (ኢሚ) ለፖሊሲና ስትራቴጂዎች ተፈጻሚነት የአተገባበር ማነዋሎች ዝግጅት ወሳኝነት አለው ያሉት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የፖሊሲና ጥናትና ምርምር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ገመቹ ጌታሁን የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር ከተተገበሩ ስራዎችን መካከል ዘርፉ የሚመራበትን የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ዝግጅት አንዱ ሲሆን ይህንንም ወደ ተግባር ለማውረድ በርካታ የስትራቴጂ ሰነዶችን ተግባር ላይ በማዋል አዎንታዊ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ለበርካታ አመታት ዘርፉ የሚመራበት የራሱ የሆነ ፖሊሲ እንዳልነበረው የገለጹት መሪ ስራ አስፈጻሚው አዲሱ የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተግባራዊ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ማስፈጻሚ ስትራቴጂዎችና ማንዋሎች እንዲሁም ጥቂቶቹ ዝርዝር ተግባር ወጥቶላቸው ወደ ተግባር ምዕራፍ የተሸጋጋሩም እንዳሉ ጠቅሰዋል፡፡
የፖሊሲ አፈጻጸም ውጤታማነቱን ለመመዘን ሰፋ ያለ የጊዜ ገደብ ይጠይቃል ያሉት ዶ/ር ገመቹ እስካሁን ባለው አካሄድ የዝግጅትና የተግባር ምዕራፍ ጎን ለጎን የተተገበረበት አግባብ ከመኖሩ ጋር ተያይዞ ዘርፉ ፈጣን ለውጦችን እያመጣ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
እንደ ሀገር ከውጪ ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የተሄደው ርቀት ፣ የኤክስፖርት ምርት በመጠን፣ በገቢ እና በአይነት እየጨመረ መምጣቱ፣ ከአቅም ልማት አንጻር እንዲሁም ዘርፉን በተመለከተ እየተሰሩ ያሉ የገጽታ ግንባታ እና ከመረጃ ተደራሽነት ስራዎች አንጻር የተገኙ ለውጦች ለስትራቴጂዎቹ ውጤታማነት አመላካች መሆናቸውን ዶ/ር ገመቹ አብራርተዋል፡፡
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የፖሊሲና ጥናትና ምርምር መሪ ስራ አስፈጻሚም ከሚያድርገው የፖሊሲና ስትራቴጂ ተግባራዊነት የክትትል ስራ ጎን ለጎን የሚወጡ ስትራቴጂዎችን በጥናትና ምርምር ስራዎች እንደሚደግፍ መሪ ስራ አሰፈጸሚው አክለዋል፡፡