አምራች ኢንዱስትሪዎች ከኢኮኖሚ እድገትና ከዜጎች የስራ እድል ፈጠራ ባሻገር ለሌሎች ዘርፎች የሚያድረጉት እገዛ ሚናው ከፍተኛ ነው (አቶ መላኩ አለበል)

ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (ኢሚ) ይህ የተገለፀው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በአስተዳደሩ ኢንዱስትሪ ዞን ወደ ስራ የገቡ አዳዲስ አምራች ኢንዱስትሪዎች የምርቃት መርሃ ግብር ላይ ነው።

የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠን ከ2018 አዲስ አመት ጀምሮ ነባር ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅና ለአዳዲሶቹ የመሰረት ድንጋይ በመጣል ላይ እንገኛለን ያሉት አቶ መላኩ አለበል በተለይም የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ፣ የጋዝ ፕሮጀክት እና ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ይፋ መሆን ከኢኮኖሚ ችግር የሚያወጣንና የብልፅግ ጉዟችንን የሚያረጋግጥ በተለይም ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ እንደ አንድ ትልቅ እድል ተደርጎ የሚወሰድ ነው ሲሉ ገልፀዋል ።

ባለፉት አመታት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት በርካታ ስራዎች ተስርተዋል ያሉት ሚኒስትሩ ለአብነትም የተደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦቶች፣ የህግ ማሻሻያዎች፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተግባራዊ መደረጉ በፌደራል ደረጃ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል መቋቋሙ እና ውጤቶች መምጣታቸውን አክለዋል ።

መንግስት ከፌደራል ጀምሮ እስከ ክልልና ከተማ አስተዳደር አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ለመደገፍ ያከናወናቸው ስራዎች ከዚህ በፊት ያልነበሩና በአዲስ መልክ ውጤት እያመጡ የሚገኙ ናቸው ያሉት አቶ መላኩ አለበል በዚህም በ2017 ዓ.ም 4.53 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉ፣ እያደገ የመጣውን የስራ እድል ፈጠራ እና የወጪ ምርት የምንዛሬ መጠን የመንግስትን ድጋፍና ክትትል ውጤት አመላካች ነው ሲሉ ገልፀዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ለኢኮኖሚያዊ እድገትና ለዜጎች ከሚፈጥረው የስራ እድል ባሻገር ለሌሎች ዘርፎች የሚያድረገው እገዛ ሚናው ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ መላኩ ለአብነትም አዲስ ከተመረቁት ኢንዱስትሪዎች መካከልም የከረጢት ማምረቻ ኢንዱስትሪው በግብርና ዘርፍ ለሚደርሰው የምርት ብክነት መቀነስና ዘርፉን በመደገፍ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ሲሉ ጠቁመዋል።

ድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ማዕከልነትዋን ለማስቀጠል ከተማ አስተዳደሩ ነባር አምራች ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ፣አዳዲስ ኢንቨስትመንት በመሳብ፣በሁሉም ዘርፍ ያሉ አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን አጠናክሮ ማስቀጠል እና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጥ ይገባል ሲሉ የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

Share this Post