በኮምቦልቻ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንቅስቃሴ አበረታች ነው (የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል)
ጥቅምት 8/2018 (ኢሚ) የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኮምቦልቻ ከተማ በሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተገኝተው የስራ ምልከታ አድርገዋል።
እንደ ሀገር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ከተደረገባቸው ክልሎች መካከል የአማራዊ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አንዱ መሆኑን የገለፁት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በኮምቦልቻ የኢንዱስትሪ መንድር ውስጥም ሆነ ውጪ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንቅስቀሴ አበረታች እንደሆነ ገልፀዋል ።
በመስክ ምልከታው በኢኮኖሚ ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ታላላቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች እየተገነቡና ይህም የተኪ ምርትንና ኤክስፖርት በማሳደግ ረገድ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልፀዋል።
ነባር አምራች ኢንዱስትሪዎቹን በተመለከተም ለዜጎች ከፍተኛ የስራ አድል በመፍጠር፣ የማምረት አቅማቸው እና የኤክስፖርት አቅማቸውን አድጎ ማየታቸው በመስክ ምልክታው ገልፀዋል።
በአጠቃላይ ገቢ ምርትን በመተካት የኤክስፖርት ተወዳዳሪነትን በማሳደግ አዳዲስ ኢንቨስትመንት ወደ ስራ በማስገባት እና ነባሩንም በማስፋት እና ተጨማሪ የስራ እድል በመፍጠር ጥሩ ስራዎች መሰራታቸውን ሚኒስትሩ ገልዋል።
የሰው ኃይል አቅርቦት፣ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥና ድጋፍ እንዲሁም የተረጋጋ ሰላም መኖሩ ኮምቦልቻን ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ተመራጭ እንደሚያደርጋትም ከአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ማረጋገጣቸውንም ሚኒስትሩ አክለው ገልፀዋል።
አምራች ኢንዱስትሪዎቹ በቀጥታ ከሚያበረክቱት ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ ጎን ለጎን ለአካባቢ ጥበቃ የሰጡት ልዩ ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት አቶ መላኩ ይህም ከአካባቢው ማህበረስብ ጋር ያላቸውን መስተጋብር ይበልጥ ጤናማ የሚያደርግ እና ለዘርፉ እድገትና ተዋዳደሪነት አስተዋፅኦ እንዳለው አክለዋል።
እነዚህና መሰል ምቹ ሁኔታዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ያሉት አቶ መላኩ እስካሁን በኮምቦልቻ ያለው የአምራች ኢንዱስትሪዎች እንቅስቃሴ አበረታችንና ሀገሪቱ ባስቀመጠችው አቅጣጫ መሰረት እየሄደ ያለ ተስፋ ሰጪ እንዲሁም ለሌሎች ክልሎች በሞዴልነት የሚጠቀስ ነው ሲሉ ገልፀዋል።