በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ ውጤቶችን የማጠናከርና ችግሮችን በመለየት ዘላቂ መፍትሔ እየተሰጠ ነው( አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ)
ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮች እና አባላት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦሌ ለሚ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንን እና ኤ ኤም ጂ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል ።
የምክር ቤት አባላቱን ተቀብለው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ እድገትና ተወዳዳሪነት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ መንግሥት ትኩረት ከሰጠባቸው ዘርፎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የኢንዱስትሪ ዘርፍ መሆኑን ገልፀው ባለፉት ዓመታት መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት በየደረጃው ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ዘርፉን ማነቆዎች መፍታት ማስቻሉን ያስረዱት አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የቆዩ በርካታ ኢንዱስትሪዎች በንቅናቄው ወደ ስራ መመለሳቸውን ገልጸዋል።
አምራች ኢንዱስትሪው በስራ ዕድል ፈጠራ ፣ ቴክኖሎጂ ችግግር እንዲሁም በውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የመሰረተ ልማት አቅርቦቶች እየተፈቱ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ዘርፉ በኢኮኖሚው ውስጥ የመሪነት ሚና እንዲኖረው ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አመላክተዋል።
በዘርፋ ያሉ ውጤቶችን የማጠናከርና ችግሮችን በመለየት ዘላቂ መፍትሔ በብሔራዊ አምራች ካውንስሉ እየተሰጠ እንደሚገኝ በመጠቆም የዘርፉን ግብ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የምክር ቤት አባላቱ ድጋፍ ክትትልና እገዛ ወሳኝ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል ።