ምግብ ማበልጸግ ከማህበረሰብ ጤና ባሻገር በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አዳዲስ የቴክኖሎጅ ፈጠራዎችን ለማስፋፋት የጎላ ሚና አለው(አቶ ተረቀኝ ቡሉልታ)
ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም(ኢ.ሚ) በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን ያሳተፈ አህጉር አቀፍ የማይክሮ ኒውትሬንት ፎረም አዲስ አበባ ተካሄደ፡፡
በመርሀ ግብሩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ እድገትና ተወዳዳሪነት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ምግብን በአስፈላጊ ማዕድናት ማበልጸግ ከማህበረሰብ ጤና ባሻገር በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ አዳዲስ የቴክኖሎጅ ፈጠራዎችን ለማስፋፋት የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡
አቶ ታረቀኝ ምግብን ማበልጸግ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ለግብርና ስራ ምቹ ለሆኑ ሀገራት በምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዕሴት እንዲጨምሩና ቀጣይነት ያለው ተወዳዳሪ ምርት እንዲያምርቱ እድል ይፈጥራል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ስነምግብና የኢንዱስትሪ እድገት ተያያዥነት አላቸው ያሉት ሚንስትር ዴኤታው የኢትዮጵያ መንግስት ምግብ ማበልጸግን ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ብሔራዊ አጀንዳዎቹ መካከል አንዱ እንደሆነ ጠቅሰው ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሌሎች ባለድርሻ መንግስታዊ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የምግብ ዘይትን ፣ ጨውና የስንዴ ዱቄትን ለማበልጸግ መጠነ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በመጨረሻም በአፍሪካ ምግብን የማበልጸግ ንቅናቄ ግቡን ይመታ ዘንድ አህጉር አቀፍ የመረጃ ፣የጥራትና የቁጥጥር ስርዓት መገንባት ለነገ የማይባል ቁልፍ ተግባር መሆኑን አሳስበዋል፡፡
መርሀ ግብሩ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ይቀጥላል፡፡