ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የህክምና ወጪን በመቀነሱ ሚሊዮኖችን ማትረፍ ችሏል።
ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም(ኢሚ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የህክምና ወጪን በመቀነሱ እና በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላሮችን በመቆጠብ አስፈላጊ የሆኑ የህክምና አቅርቦቶችን በአገር ውስጥ በመመረት ላይ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ገልፀዋል፡፡
በተለይም ከውጭ በሚገቡ የህክምና አቅርቦቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት በእጅጉ በመቀነሱ ሀገሪቱን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የውጭ ምንዛሪ ታድጋለች ብለዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ባለፉት ሶስት አመታት የተካሄደው ማሻሻያ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገር ውስጥ የሚመረተው የህክምና ግብአት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ቁጠባ እየፈጠረ ነው ያሉት ሚኒስትሩ የብሄራዊ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል የፋይናንስ አቅርቦትን በማሳደግ፣ የውጭ ምንዛሪ ስራዎችን በማሳለጥ፣ መሠረተ ልማቶችን በማሻሻል እና የሀገር ውስጥ አምራቾች የገበያ ትስስርን በማስፋት የተገኘውን ውጤት ለማጠናከር እየሰራ ነው፡፡