የአምራች ኢንዱስትሪውን አመራር ሳይንሳዊ በማድረግ አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ ተወዳደሪነትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው
ታህሳስ17/2018 ዓ.ም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች የኢንዱስትሪዎቹን የሚመሩበት ቁመናን የሚያሳይ ሳይንሳዊ ጥናት በማቅረብ ውይይት አካሄደ፡፡
የኢንዱስትሪ አመራርን በማዘመን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ምርታማነት በማሻሻል አለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ከፍ ለማድረግ ታስቦ በተካሄደው ጥናት በኢንዱስትሪ ብሔራዊ ካውንስል ተመርጠው ክትትልና ድጋፍ የሚሰጥባቸው 44 የሚሆኑ የቴክስታይልና ጋርመንት፣ የኬሚካል እና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ፣የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ የምግብና መጠጥ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ እና ኢንጂነሪግ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተካተዋል፡፡
በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሃገራችን ውስጥ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ኢንዱስትሪዎቻችን የአስተዳደርና የተማረ የሰው ሃይል እጥረት እንዳለባቸው የገለጹት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የአመራር ችግሮችን ሳይንሳዊ በሆኑ ጥናቶች በመለየትና ተግባራዊ በማድረግ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን አለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም በጥናቱ የተሻለ ቁመና ላይ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ውጤታቸውን እንዲያስቀጥሉ እና በጥናቱ የተገለጸው ውጤት በኤክስፖርት እና በምርት መገለጽ እንዳለበት እና በተደረገው ጥናት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ አምራች ኢንዱስትሪዎች በፍጥነት ወደስራ በመግባት ደረጃቸውን እንዲያሻሽሉ አሳስበው በኢንዱስትሪ ካውንስሉ በኩል መፈታት የሚገባቸውን ካውንስሉ በአፋጣኝ እንደሚፈታ ግልጸዋል፡፡