የዲጂታላይዜሽን ሽግግር የአምራች ኢንዱስትሪውን የምርት ጥራት እና ተወዳዳሪነት ያሳድጋል

ታህሳስ 21/2018 ዓ.ም (ኢሚ) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የአምራች ኢንዱስትሪውን የምርት ጥራት እና ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገልጸዋል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ መነሻነት የአምራች ኢንዱስትሪ ምርታማነትን ማሻሻል የሚያስችል መሠረት መጣሉን ያነሱት ሚኒስትሩ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ደግሞ በቀጣይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ተወዳዳሪ አምራች ኢንዱስትሪ ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አክለዋል።

የዲጂታላይዜሽን ሽግግር የኢንዱስትሪ ምርት ጥራት እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን በማስጠበቅ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማሳለጥ የማይተካ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ማጠናቀቂያ እና የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱ ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት፥ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ተደራሽነትን ማስፋት፣ ለዜጎች እኩል ዕድል መፍጠር እንዲሁም የዜጎች እና የተቋማትን መተማመን ማጎልበት ቁልፍ ትልሞች መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዚህም የሕዝብ ዲጂታል መሠረተ ልማቶችን በማስፋት የዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮ በሰው ተኮር ዲጂታል ሥርዓት ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

Share this Post