ዓለም በፈጣን የለውጥ ሂደት ላይ ስለሆነች የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲዎች በየጊዜው ወቅቱን ባማከለ ሁኔታ መሻሻል አለባቸው

ታህሳስ 28/2018 ዓ.ም(ኢ.ሚ) በኢፌድሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርስቲ መካከል አብሮ መስራት የሚያስችል የስምምነት ሰነድ ተፈረመ፡፡

በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ ዕድገትና ተወዳዳሪነት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ ዓለም በፈጣን የለውጥ ሂደት ላይ ስለሆነች የአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲዎች በየጊዜው ወቅቱን ባማከለ ሁኔታ መሻሻል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

አቶ ታረቀኝ ዩኒቨርስቲው ለአምራች ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ማሻሻያ የሚሆኑ ጥናትና ምርምሮችን በትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተለይም አዳዲስ የሀይል አማራጮችን ከማመላከት አኳያ፣የዑደታዊ ኢኮኖሚ አሰራርን በተመለከተና ለአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተር ፕራይዞች የአዋጭነት ጥናት በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ስራ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ጨምሮ በርካታ ኤክስፖርትን የሚያነቃቁ ተግባራትን እያከናወነ ነው ያሉት ሚንስትር ዴኤታው ዩኒቨርስቲው እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ለማጠናከር ለዘርፉ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስራ እንዲሰራና የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ማነቆዎች የሚፈቱ ጥናትና ምርምሮችን ከማድረግ አኳያ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቱ በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርስቲ ፕሬዜዳንት ዶ/ር ለሚ ጉታ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲው ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በትብብር ለመስራት ተቋማዊ ሀላፊነት እንዳለው በመጥቀስ የአምራች ኢንዱስትሪ መሪዎችን ለማብቃት ራሱን የቻለ የስልጠና መርሀ ግብር ቀርፆ በማስተርስና በፒ ኤች ዲ ደረጃ ስልጠና እየሰጠ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ዶ/ር ለሚ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችም ለዩኒቨርስቲው ተማሪዎች መጥተው ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት ሁኔታ እንዲኖር የተቋማቸው ፍላጎት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም ዩኒቨርስቲውና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተፈራረሙት የስምምነት ሰነድ የኢንዱስትሪ ቴክኖሎጅ ሽግግርን እንደሚያሳልጥ የፊርማ ስነ ስርዓቱን የተሳተፉ የሁለቱም ተቋማት ምሁራን አብራርተዋል፡፡

Share this Post