መንግስት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን ለማጠናከርና ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ እንዲፈጠር አበክሮ እየሰራ ነው(አቶ መላኩ አለበል)
ጥር 4/2018 ዓ.ም (ኢ.ሚ)የኢፌድሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የጃፓን ከፍተኛ ባለስልጣናትንና የኢንቨስትመንት ልኡካንን ተቀብሎ አወያየ፡፡
ውይይቱን የመሩት የኢንዱስትሪ ሚንስትር አቶ መላኩ አለበል መንግስት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚሰማሩ ሀገር በቀልና የውጭ ባለሀብቶችን ለማጠናከርና በዘርፉ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ እንዲፈጠር አበክሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አቶ መላኩ የኢትዮጵያ መንግስት የዘርፉን ባለሙያዎች ክህሎት በመገንባት፣የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋምና የተለያዩ ዘርፉን የሚያነቃቁ ስልቶችን በመንደፍ የሀገር ውስጥ ኢንተር ፕራይዞችን የሚደግፉ የፈጠራ ስራዎች የሚሰሩበትን ዐውድ እየፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ልክ እንደ ጃፓን የሰው ሀይልና የቴክኖሎጅ ልህቀት መሳ ለመሳ የሚሄዱበትን ሁኔታ ለመፍጠር ትፈልጋለች ያሉት ሚንስትሩ ሀገራቸው ከጃፓን ጋር የሁለትዮሽ የኢንዱስትሪ ትብብር እንዲኖር ፍላጎት እንዳላት አስረድተዋል፡፡
በተለይ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተለይተው ትኩረት በተሰጣቸው እንደ አግሮ ፕሮሰሲንግና ቆዳ በመሳሰሉት ዘርፎች የጃፓን ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን ቢያፈሱ መልካም መሆኑን አስገንዝበዋል ።
በተጨማሪም ከኢትዮጵያ አምራች ኢንዱስትሪ ማነቆዎች መካከል ዋነኛው የኢንቨስትመንት ባንክ አለመኖር መሆኑን ጠቅሰው ጃፓናዊያን ባለሀብቶች በዘርፉ ቢሰማሩ ጥሩ እንደ ሆነ ጠቁመዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ኢትዮጵያ ያሏት የኢንቨስትመንት አማራጮች አንድ በአንድ ለተሳታፊዎች የተገለጹ ሲሆን የጃፓን ልዑካንም ሀገሪቱ ባሏት ምቹ ሁኔታዎች ተደስተው በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት ለማድረግ መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡