የፖሊሲ ባንኮች ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ ይበልጥ ለማጠናከር ዘመኑን የዋጀ አቅም ሊኖራቸው ይገባል(አቶ መላኩ አለበል)

ጥር1/2018 ዓ.ም(ኢ.ሚ)የኢፌዴሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስራ ሶስት ግዙፍ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የብድር አቅርቦትን በተመለከተ አወያየ፡፡

ውይይቱን የመሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ መላኩ አለበል የፖሊሲ ባንኮች እስካሁን ለአምራች ኢንዱስትሪው ያደረጉት ድጋፍ ጥሩ ቢሆንም ከዚህ የበለጠ መስራት የሚያስችል ዘመኑን የዋጀ አቅም መፍጠር እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡

አቶ መላኩ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ባንኮች ባለመኖራቸው ምክንያት ሁሉም አምራች ኢንዱስትሪዎች ከፖሊሲ ባንኮች እንደ ልብ ብድር የማግኘት ክፍተት መኖሩን በመጥቀስ አንዳንድ ባለሀብቶች ፋብሪካ ለመገንባት መሬት ከተፈቀደላቸው በኋላ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ስራ ለመጀመር የሚያደርጉት መዘግየት ከሀገር ኢኮኖሚ አኳያ ያለውን ጉዳት ተገንዝቦ ባንኩ የአገልግሎት ቅልጥፍናውን ማዘመን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በውይይት መርሀ ግብሩ የተሳተፉ የአምራች ኢንዱስትሪ ተወካዮች ባንኩ የሚቀርብለትን የአዋጭነት ጥናት ተመልክቶ ፈጥኖ ምላሽ አለመስጠቱንና ለብድር ማስያዣነት የሚገምተው ግምት የሚዛናዊነት ክፍተት እንዳለበት አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዜዳንት አቶ ደረጀ ፉፋ ደንበኞች የባንኩን የአሰራር መመሪያ በጥልቅ ባለመረዳት ችግር ምክንያት በአንዳንድ ጉዳዮች ባንኩን ያለአግባብ የመውቀስ ሁኔታዎች እንዳሉ ገልፀዋል፡፡

አክለውም ንግድ ባንክ ይህንን ችግር ለመቅረፍ ወደ ፊት ለደንበኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪዎች ብድር ለማግኘት የሚያቀርቡት የአዋጭነት ጥናት ጥራቱን የጠበቀ ካለመሆኑም በላይ ከሌላ ዘርፍ በቀጥታ የተገለበጡ ናቸው ያሉት ምክትል ፕሬዜዳንቱ ንግድ ባንክ መሰል ችግሮችን ለመቅረፍና የብድር አሰጣጥ ሂደትን ቀልጣፋ ለማድረግ የሰው አልባ አስተውሎት አሰራርን ለመተግበር እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር በየጊዜው ለመቅረፍ በየፋብሪካዎች የተናጠል ጉብኝት ከማድረግ ጀምሮ በርካታ ችግር ፈች የውይይት መድረኮችንና የንቅናቄ ሁነቶችን እያዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።

Share this Post