መንግስት የቆዳ ኢንዱስትሪ ማነቆዎችን ለመፍታት አሳሪ የሆኑ ፖሊሲዎችን ከማሻሻል ባሻገር ለዘርፉ ባለሀብቶች በርካታ ድጋፎችን እያደረገ ነው(አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ)
ጥር 13/2018 ዓ.ም(ኢ.ሚ)የኢፌድሪ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ከቆዳ ኢንዱስትሪ ባለሀብቶች ጋር በአዲሱ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ልማትና ግብይት ረቂቅ አዋጅ ላይ የውይይት መድረክ አካሄደ፡፡
ውይይቱን የመሩት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ ዕድገትና ተወዳዳሪነት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ መንግስት የቆዳ ኢንዱስትሪ ማነቆዎችን ለመፍታት አሳሪ የሆኑ ፖሊሲዎችን ከማሻሻል ባሻገር ለዘርፉ ባለሀብቶች በርካታ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑን ገልፀው አሁን ላይ በዘርፉ እየታዩ ያሉ እመርታዎች እንዳሉ አብራርተዋል፡፡
ፖሊሲዎች፣ አዋጆችና መመሪያዎችን የብዙኃኑን እንጅ የእያንዳንዱን ግለሰብ ፍላጎት መሰረት ሊያደርጉ አይችልም ያሉት ሚንስትር ዴኤታው እያንዳንዱን ችግር ለመፍታት የዘርፉ ተዋንያን ሁሉንም ነገር ከመንግስት ሳይጠብቁ በራሳቸው አቅም ለመፍታት መጣር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በተጨማሪም አሁን የተጀመረውን ረቂቅ አዋጅ ለሁሉም አምራች ኢንዱስትሪ ምቹ ሆኖ እንዲወጣ የዘርፉ ማህበራት በህብረት ተወያይተው የማጠናከር ስራ እንዲሰሩ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
በሌላ በኩል የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሽ ለማ ከዚህ በኋላ እንደ ሀገር አንድም የሚጣል ቆዳ እንዳይኖርና የዕሴት ጭማሪ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
የመርሀ ግብሩ ዋና ዓላማ ጥሬ ቆዳ ጥራቱ ተጠብቆ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት እንዲውል በየደረጃው ያሉ የዘርፉ ተዋንያን የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት የሚወጡበት ሁኔታ እንዲፈጠር ለረቂቅ አዋጁ ተጨማሪ ግብዓት ለማሰባሰብ እንደሆነ ተገልጿል ፡፡
በረቂቅ አዋጁ ክለሳ ሂደት የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትን ጨምሮ የሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማትና የዘርፍ ማህበራት የተሳተፉበት ሲሆን ረቂቅ አዋጁም አሁን ላይ የዓለም ገበያ የሚፈልገውን ጥራት ያለው ጥሬ ቆዳና ሌጦ በማቅረብ በቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሀገሪቱ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማስቻል እንደሆነ ተገልጿል ፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ የዘርፍ ማህበራት መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት መደሰታቸውን ገልጸው ረቂቅ አዋጁ ላይ አንዳንድ መስተካከልና መካተት ያለባቸው ነገሮች እንዲስተካከሉ ግብዓት ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም በውይይቱ የተነሱ ገንቢ ሀሳቦችን እንደ ግብዓት በመውሰድ የማስተካከያ ሀሳቦች በረቂቅ አዋጁ እንደሚካተቱ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡